ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 6:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ አራቱ ቆመው ከነበሩበት ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት የወጡ የሰማይ መናፍስት ናቸው።

6. የባለ ዱሪ ፈረሶች ወደ ሰሜን፤ የባለ አምባላይ ፈረሶች ወደ ምዕራብ አገር፣ የባለ ዥንጒርጒር ፈረሶች ወደ ደቡብ አገር ይወጣል።”

7. ጠንካሮቹ ፈረሶች ሲወጡ፣ በምድር ሁሉ ለመመላለስ አቈብቍበው ነበር። እርሱም፣ “ወደ ምድር ሁሉ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ሄዱ።

8. ከዚያም ጮኾ እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ወደ ሰሜን አገር የሚወጡት፣ መንፈሴን በሰሜን ምድር አሳርፈውታል።”

9. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

10. “ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ ከዮዳኤም ወርቅና ብር ውሰድ፤ በዚያው ቀን ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ።

11. ወርቁንና ብሩን ወስደህ አክሊል ሥራ፤ በኢዮሴዴቅ ልጅ በሊቀ ካህኑ በኢያሱ ራስ ላይም አድርገው፤

12. ለእርሱም እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እነሆ፤ ስሙ ቅርንጫፍ የተባለው ሰው ይህ ነው፤ እርሱም በቦታው ይንሰራፋል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ይሠራል።

13. የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው፤ ክብርን ይጐናጸፋል፤ በዙፋኑ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል ስምምነት ይኖራል።

14. አክሊሉም ለሔሌምና ለጦብያ፣ ለዮዳኤና ለሶፎንያስ ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መታሰቢያ ይሆናል።

15. እነዚያ በሩቅ ያሉት መጥተው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲሠራ ያግዛሉ፤ እናንተም እግዚአብሔር ጸባኦት እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በጥንቃቄ ብትታዘዙ ይህ ይሆናል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘካርያስ 6