ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በራሪው የመጽሐፍ ጥቅልል

1. እንደ ገናም ተመለከትሁ፤ በዚያም በፊቴ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አየሁ።

2. እርሱም፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም፣ “ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ ዐሥር ክንድ የሆነ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አያለሁ” አልሁት።

3. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ይህ በምድር ሁሉ ላይ የሚወጣ ርግማን ነው፤ በአንደኛው በኩል እንደ ተጻፈው የሚሰርቅ ሁሉ ይጠፋል፤ በሌላው በኩል ደግሞ እንደ ተጻፈው በሐሰት የሚምል ሁሉ ይጠፋልና።

4. እግዚአብሔር ጸባኦት ‘እኔ ርግማኑን አመጣዋለሁ፤ እርሱም ወደ ሌባው ቤትና በስሜ በሐሰት ወደሚምለው ሰው ቤት ይገባል፤ በዚያም ይቀመጣል፤ ቤቱን፣ እንጨቱንና ድንጋዩን ያጠፋል ይላል።”

በቅርጫት ውስጥ ያለች ሴት

5. ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወደ እኔ መጥቶ፣ “ወደ ላይ ተመልከት፤ ይህ የሚመጣው ምን እንደሆነ እይ” አለኝ።

6. እኔም፣ “ምንድን ነው?” አልሁት። እርሱም፣ “የኢፍ መስፈሪያ ነው” አለኝ። ቀጥሎም “ይህ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ያለው የሕዝቡ በደል ነው” አለኝ።

7. ከዚያም ከእርሳስ የተሠራው ክዳን ተነሣ፤ የኢፍ መስፈሪያ ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር።

8. እርሱም፣ “ይህች ርኵሰት ናት” ብሎ ወደ ኢፍ መስፈሪያ መልሶ አስገባት፤ የእርሳሱንም ክዳን ወደ ቅርጫቱ አፍ ገፍቶ ገጠመው።

9. ከዚያም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ እነሆም፣ ከፊቴ ሁለት ሴቶች ነበሩ፤ በክንፎቻቸውም ነፋስ ነበር፤ ክንፎቻቸውም እንደ ሽመላ ክንፎች ነበሩ፤ የኢፍ መስፈሪያውንም በምድርና በሰማይ መካከል አነሡት።

10. ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውንም መልአክ፣ “ቅርጫቱን የሚወስዱት ወዴት ነው?” አልሁት።

11. እርሱም፣ “ቤት ሊሠሩለት ወደ ባቢሎን ምድር ይወስዱታል፤ በተዘጋጀም ጊዜ ወስደው በቦታው ያስቀምጡታል” አለኝ።