ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለሊቀ ካህኑ የሚሆን ንጹሕ ልብስ

1. እርሱም ሊቀ ካህኑን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ፣ ሰይጣንም ሊከሰው በስተ ቀኙ ቆሞ አሳየኝ።

2. እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አንተ ሰይጣን፤ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ይህ ሰው ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን?” አለው።

3. ኢያሱም ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር።

4. መልአኩም ከፊቱ ቆመው የነበሩትን፣ “ያደፉ ልብሶቹን አውልቁለት” አላቸው።ኢያሱንም፣ “እነሆ፤ ኀጢአትህን ከአንተ አስወግጃለሁ፤ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ” አለው።

5. እኔም፣ “ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉለት” አልሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ እያለ፣ ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አደረጉለት፤ ልብስም አለበሱት።

6. የእግዚአብሔርም መልአክ ለኢያሱ ይህን ማስጠንቀቂያ ሰጠው፤

7. “እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በመንገዴ ብትሄድ፣ ትእዛዜንም ብትጠብቅ፣ ቤቴን ታስተዳድራለህ፤ በአደባባዮቼም ላይ ኀላፊ ትሆናለህ፤ በዚህ በቆሙት መካከል ቦታ እሰጥሃለሁ።

8. “ ‘ሊቀ ካህኑ ኢያሱ ሆይ፤ ስማ፤ በፊትህ የሚቀመጡትም ረዳቶችህ ገና ወደ ፊት ለሚመጡት ምልክት የሚሆኑ ሰዎች ናቸውና ይስሙ፤ እነሆ፤ ባሪያዬን ቊጥቋጡን አመጣለሁ።

9. በኢያሱ ፊት ያስቀመጥሁት ድንጋይ እነሆ! በዚያ በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዐይኖች አሉ፤ በእርሱም ላይ ቅርጽ እቀርጻለሁ፤ የዚህችንም ምድር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

10. “ ‘በዚያን ቀን እያንዳንዱ በገዛ ወይኑና በለሱ ሥር ሆኖ ባልንጀራውን ይጋብዛል፤’ ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።