ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 14:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ምድር ሁሉ ከጌባ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሬሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች።

11. የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች።

12. እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጒድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ።

13. በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል።

14. ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል።

15. ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችን፣ በቅሎዎችን ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሶች ሁሉ ይመታል።

16. ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ።

17. የምድር ሕዝብ ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ከሆነ ዝናብ አያገኙም።

18. የግብፅም ሰዎች ወደዚያ ሳይወጡ ቢቀሩ፣ ዝናብ አያገኙም፤ እግዚአብሔር ወጥተው የዳስ በዓልን በማያከብሩ አሕዛብ ላይ የሚያደርሰውን መቅሠፍት በእነርሱም ላይ ያመጣል።

19. የዳስን በዓል ወጥተው ለማያከብሩ ግብፃውያንና አሕዛብ ሁሉ የተወሰነው ቅጣት ይህ ነው።

20. በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር” የሚል ጽሑፍ ይቀረጻል፤ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የማብሰያ ምንቸቶች ከመሠዊያው ፊት ለፊት እንዳሉ ሳሕኖች የተቀደሱ ይሆናሉ።

21. በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸባኦት የተቀደሱ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚመጡ ሁሉ ምንቸቶቹን በመውሰድ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያን ቀን በእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ከነዓናዊ አይገኝም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘካርያስ 14