ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 11:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሊባኖስ ሆይ፤ እሳት ዝግባሽን እንዲ በላው፣ደጆችሽን ክፈቺ!

2. የጥድ ዛፍ ሆይ፤ ዝግባ ወድቋልና አልቅስ፤የከበሩትም ዛፎች ጠፍተዋል!የባሳን ወርካዎች ሆይ፤ አልቅሱ፤ጥቅጥቅ ያለው ደን ተመንጥሮአል!

3. የእረኞችን ዋይታ ስሙ፤ክብራቸው ተገፎአልና፤የአንበሶችን ጩኸት ስሙ፤ጥቅጥቅ ያለው የዮርዳኖስ ደን ወድሟል!

4. እግዚአብሔር አምላኬ እንዲህ ይላል፤ “ለዕርድ የተለዩትን በጎች አሰማራ፤

5. የገዟቸው ያርዷቸዋል፤ ሳይቀጡም ይቀራሉ፤ የሸጧቸውም፣ ‘እግዚአብሔር ይመስገን፤ ባለጠጋ ሆኛለሁ’ ይላሉ፤ ጠባቂዎቻቸውም እንኳ አይራሩላቸውም።

6. ከእንግዲህ በምድሪቱ ለሚኖረው ሕዝብ አልራራምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ምድሪቱን ያስጨንቃሉ፤ እኔም ከእጃቸው አላድናቸውም።”

7. ስለዚህ ለዕርድ የተለዩትን በጎች፣ በተለይም የተጨቈኑትን አሰማራሁ። ሁለት በትሮች ወስጄም፣ አንዱን “ሞገስ” ሌላውንም “አንድነት” ብዬ ጠራኋቸው፤ መንጋውንም አሰማራሁ።

8. በአንድ ወር ውስጥ ሦስቱን እረኞች አስወገድሁ።በጎቹ ጠሉኝ፤ እኔም፣ ሰለቸኋቸው፤

9. “እረኛችሁ አልሆንም፤ የሚሞቱት ይሙቱ፤ የሚጠፉት ይጥፉ፤ የቀሩትም አንዱ የሌላውን ሥጋ ይብላ” አልኋቸው።

10. ከዚያም ከአሕዛብ ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን ለማፍረስ፣ “ሞገስ” ብዬ የጠራሁትን በትሬን ወስጄ ሰበርሁት።

11. በዚያም ቀን ኪዳኑ ፈረሰ፤ ሲመለከቱኝ የነበሩትና የተጨነቁት በጎችም የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ዐወቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘካርያስ 11