ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 1:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ ሳባጥ በሚባለው በዐሥራ አንደኛው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

8. በምሽት ራእይ አየሁ፤ እዚያም በፊቴ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ላይ ተቀምጦአል፤ እርሱም በሸለቆ ውስጥ በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ነበር፤ ከበስተ ኋላውም መጋላ፣ ሐመርና አንባላይ ፈረሶች ነበሩ።

9. እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁ።ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክም፣ “እነዚህ ምን እንደሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ።

10. ከዚያም በባርሰነት ዛፎች መካከል የቆመው ሰው፣ “እነዚህ በምድር ሁሉ እንዲመላለሱ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው” ሲል መለሰ።

11. እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ለነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፣ “በምድር ሁሉ ተመላለስን፤ መላዋ ምድርም ዐርፋ በሰላም ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት።

12. ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ፣ “እግዚአብሔር ጸባኦት ሆይ፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥ የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ።

13. እግዚአብሔርም ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መለሰለት።

14. ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ተናገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ጽዮንና ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ ቀንቻለሁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘካርያስ 1