ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 1:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

2. “እግዚአብሔር በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር፤

3. ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ “እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤ እግዚአብሔር ጸባኦት፤

4. የቀደሙት ነቢያት፣ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት፣ “ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ’ ይላል በማለት ለአባቶቻችሁ ሰብከው ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙም፤ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፤ ይላል እግዚአብሔር።

5. አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያትስ ለዘላለም በሕይወት ይኖራሉን?

6. ለባሪያዎቼ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃልና ሥርዐት በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሰምን?“እነርሱም ንስሓ ገብተው፤ እንዲህ አሉ፤ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት በወሰነው መሠረት፣ ለሥራችንና ለመንገዳችን የሚገባውን አድርጎብናል።’ ”

7. ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ ሳባጥ በሚባለው በዐሥራ አንደኛው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

8. በምሽት ራእይ አየሁ፤ እዚያም በፊቴ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ላይ ተቀምጦአል፤ እርሱም በሸለቆ ውስጥ በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ነበር፤ ከበስተ ኋላውም መጋላ፣ ሐመርና አንባላይ ፈረሶች ነበሩ።

9. እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁ።ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክም፣ “እነዚህ ምን እንደሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘካርያስ 1