ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 9:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ምድረ በዳ ተናገረው፤ እንዲህም አለው፤

2. “እስራኤላውያን በተወሰነው ጊዜ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ አድርግ፤

3. በዓሉንም በዚህ ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በተወሰነው ሕግና ሥርዐት መሠረት ሁሉ አክብሩ።”

4. ስለዚህ ሙሴ ፋሲካን እንዲያከብሩ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤

5. እነርሱም በመጀመሪያው ወር፣ በዐሥራ አራተኛውም ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካ አደረጉ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉንም አደረጉ።

6. አንዳንዶቹ ግን የሰው ሬሳ በመንካታቸው በሥርዐቱ መሠረት ረክሰው ስለ ነበር በዚያን ዕለት የፋሲካን በዓል ማክበር አልቻሉም፤ ስለዚህም በዚያኑ ዕለት ወደ ሙሴና ወደ አሮን መጥተው፣

7. ሙሴን፣ “በሬሳ ምክንያት ረክሰናል፤ ታዲያ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነን በተወሰነው ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” አሉት።

8. ሙሴም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ የሚያዘውን እስካውቅ ድረስ ጠብቁ” ሲል መለሰላቸው።

9. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

10. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከእናንተ ወይም ከዘሮቻችሁ ማንኛውም ሰው በሬሳ ምክንያት ቢረክስ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ፋሲካ ማክበር ይችላል፤

11. ይህንም በሁለተኛው ወር፣ በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ያክብሩ፤ የፋሲካውንም በግ እርሾ ከሌለበት ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 9