ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 5:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ወንድም ሆነ ሴት አስወጡ፤ እኔ በመካከላቸው የምኖርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈር አስወጧቸው።”

4. እስራኤላውያን ይህንኑ አደረጉ፤ ሰዎቹንም ከሰፈር አስወጧቸው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘውም መሠረት ፈጸሙ።

5. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

6. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ወንድም ሆነ ሴት በማናቸውም ረገድ ሌላውን ቢበድልና ከዚህም የተነሣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ያለውን ታማኝነት ቢያጐድል ያ ሰው በደለኛ ነው

7. በሠራው ኀጢአት ይናዘዝ፤ ሰለበደሉም ሙሉ ካሳ ይክፈል፤ የተመደበበትም ካሳ ላይ አንድ አምስተኛ በመጨመር በደል ላደረሰበት ሰው ይስጥ፤

8. ነገር ግን ይህ ሰው ካሳውን የሚቀበልለት ዘመድ ከሌለው ካሳው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለሚሆን ማስተስረያ እንዲሆነው ከሚያቀርበው አውራ በግ ጋር ለካህኑ ይስጥ።

9. እስራኤላውያን የሚያመጧቸው የተቀደሱ ስጦታዎች ሁሉ ለተቀባዩ ካህን ይሆናሉ፤

10. የእያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ ስጦታ ለካህኑ ይሆናል፤ ለካህኑ የሚሰጠውም ሁሉ የራሱ ይሆናል።’ ”

11. ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

12. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘አንዲት ባለ ትዳር ሴት ወደ ሌላ ወንድ በማዘንበል ለባሏ ያላትን ታማኝነት አጒድላ፣

13. ከሌላ ሰው ጋር ብትተኛ፣ ይህም እጅ ከፍንጅ ባለመያዟ ምክንያት ይህ ከባሏ ቢደበቅ፣ የሚመሰክርባት ሰው ባይኖርና መርከሷም ባይገለጥ፣

14. ባሏ የቅናት መንፈስ አድሮበት ቢጠረጥርና በርግጥም ጐድፋ ብትገኝ ወይም ባሏ የቅናት መንፈስ አድሮበት ቢጠረጥርና እርሷ ግን ጐድፋ ባትገኝ፣

15. ወደ ካህኑ ይውሰዳት፤ ስለ እርሷም አንድ ኪሎ ገብስ ዱቄት ለቊርባን ይውሰድ፤ በላዩ ላይ ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት፤ ይህ ስለ ቅናት የቀረበ የእህል ቊርባን በደልን የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና።

16. “ ‘ካህኑ ሴትየዋን ያመጣትና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንድትቆም ያደርጋታል፤

17. ከዚያም የተቀደሰ ውሃ በሸክላ ዕቃ ቀድቶ በማደሪያው ድንኳን ካለው ወለል ጥቂት ዐፈር ቈንጥሮ በውሃው ውስጥ ይጨምራል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 5