ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 35:24-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. ማኅበሩ በዚህ ሰውና በደመኛው መካከል በእነዚህ ደንቦች መሠረት ይፍረድ።

25. ማኅበሩም በነፍሰ ገዳይነት የተከሰሰውን ሰው ከደመኛው እጅ በማስጣል ወደ ሸሸበት ወደ መማጸኛው ከተማ ይመልሰው፤ የተቀደሰ ዘይት የተቀባው ሊቀ ካህን እስኪሞትም ድረስ በዚያ ይቈይ።

26. “ ‘ሆኖም ተከሳሹ ሰው ሸሽቶ ከተጠጋበት መማጸኛ ከተማ ክልል ከወጣ፣

27. ደም ተበቃዩም ከከተማው ውጭ ካገኘው፣ ተከሳሹን ሊገድለው ይችላል፤ በነፍሰ ገዳይነትም አይጠየቅም።

28. ተከሳሹም ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛው ከተማ ይቈይ፤ ወደ ገዛ ርስቱ መመለስ የሚችለው ከሊቀ ካህናቱ ሞት በኋላ ብቻ ነው።

29. “ ‘እንግዲህ በየትኛውም በምትኖሩበት ስፍራ፣ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ የምትፈጽሟቸው ሕጋዊ ግዴታዎቻችሁ እነዚህ ናቸው።

30. “ ‘ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው በሞት የሚቀጣው ምስክሮች ሲመሰክሩበት ብቻ ነው፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው በአንድ ምስክር ብቻ በሞት አይቀጣም።

31. “ ‘በሞት መቀጣት ስላለበት ሰው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ ፈጽሞ መሞት አለበት።

32. “ ‘ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ ስለ ገባ ስለማንኛውም ሰው የደም ዋጋ በመቀበል ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ አገሩ ተመልሶ ሄዶ እዚያ እንዲኖር አታድርጉ።

33. “ ‘ደም ምድሪቱን ስለሚያረክሳት፣ ደም ለፈሰሰባትም ምድር ስርየት ሊደረግላት የሚችለው በሌላ ሳይሆን በዚያው ደሙን ባፈሰሰው ሰው ደም ብቻ በመሆኑ፣ የምትኖሩባትን ምድር በደም አታርከሷት፤

34. የምትኖሩባትን፣ እኔም የማድርባትን ምድር አታርክሷት እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁና።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 35