ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 32:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. “ይህን ባታደርጉ ግን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ትበድላላችሁ፤ ኀጢአታችሁ እንደሚያገኛችሁም ዕወቁ።

24. ለሴቶቻችሁና ለልጆቻችሁ ከተሞች፣ ለበግና ለፍየል መንጎቻችሁም ጒረኖች ሥሩላቸው፤ የገባችሁበትን የተስፋ ቃል ግን ፈጽሙ።”

25. የጋድና የሮቤል ሰዎች ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን ያዘዘንን እንፈጽማለን።

26. ልጆቻችንና ሚስቶቻችን፣ የበግና የፍየል እንዲሁም የከብት መንጎቻችን እዚሁ በገለዓድ ከተሞች ይቀራሉ፤

27. ባሮችህ ግን ልክ ጌታችን እንዳለው እያንዳንዱ ሰው ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመዋጋት እንሻገራለን።”

28. ከዚያም ሙሴ ለካህኑ ለአልዓዛር፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ነገድ ቤተ ሰብ አለቆች እነርሱን አስመልክቶ ትእዛዝ ሰጠ፤

29. እንዲህም አላቸው፤ “የጋድና የሮቤል ወንድ ሁሉ፣ እያንዳንዱ ለጦርነት በመዘ ጋጀት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ከእናንተ ጋር ዮርዳኖስን የሚሻገር ከሆነ፣ ምድሪቱም በእጃችሁ ስትገባ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ስጧቸው።

30. ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋር ካልተሻገሩ ግን፣ ርስታቸውን አብረዋችሁ በከነዓን መካፈል አለባቸው።”

31. የጋድና የሮቤል ሰዎች እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ባሪያዎችህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ያደርጋሉ፤

32. ለጦርነት ዝግጁ ሆነን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወደ ከነዓን እንሻገራለን፤ የምንወርሰው ርስት ግን ከዮርዳኖስ ወዲህ እዚሁ ይሆናል።”

33. ከዚያም ሙሴ፣ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛትና የባሳንን ንጉሥ የዐግን ግዛት ማለትም ምድሪቱንና ከነከተሞቿ በዙሪያዋ ያለውን ግዛት በሙሉ ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለዮሴፍ ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጣቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 32