ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 32:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እጅግ ብዙ የሆነ የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች የነበሩአቸው የሮቤልና የጋድ ነገዶች የኢያዜርና የገለዓድ ምድር ለከብት ምቹ ስፍራዎች መሆናቸውን አዩ።

2. ስለዚህ ወደ ሙሴ፣ ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ማኅበረ ሰቡ መሪዎች መጥተው እንዲህ አሉ፤

3. “አጣሮት፣ ዲቦን፣ ኢያዜር፣ ኒምራ፣ ሐሴቦን፣ ኤልያሊ፣ ሴባማ፣ ናባውና፣ ባያን፣

4. እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ሕዝብ ፊት እንዲሸነፍ ያደረገው ይህ ሁሉ ምድር ለከብት ምቹ ነው፤ እኛ አገልጋዮችህም ከብቶች አሉን።

5. በፊትህ ሞገስ ያገኘን ከሆነ ይህ ምድር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በርስትነት ይሰጠን፤ ዮርዳኖስንም እንድንሻገር አታድርገን።”

6. ሙሴም የጋድንና የሮቤልን ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወገኖቻችሁ ወደ ጦርነት ይሂዱ?

7. እስራኤላውያን ተሻግረው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጧቸው ለምድን ነው?

8. አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜም ያደረጉት ይህንኑ ነበር።

9. ወደ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ካዩ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ እስራኤላውያንን ተስፋ አስቈረጧቸው።

10. በዚያም ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 32