ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 31:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ሙሴም ከጦርነት በተመለሱት በሰራዊቱ አዛዦች ማለትም በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።

15. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሴቶችን ሁሉ እንዴት በሕይወት ትተውአቸዋላችሁ?”

16. የበለዓምን ምክር ተቀብለው በፌጎር በተፈጸመው ድርጊት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲመለሱና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ሕዝብ እንዲቀሠፍ ያደረጉት እነርሱ ናቸው።

17. አሁንም ወንዶቹን ልጆች ሁሉ፣ ወንድ ያወቊትንም ሴቶች በሙሉ ግደሉዋቸው፤

18. ነገር ግን ወንድ ያላወቁትን ልጃገረዶች ሁሉ ለራሳችሁ አስቀሩአቸው።

19. “ከእናንት መካከል ሰው የገደለ ወይም የተገደለውን የነካ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ይቈይ። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና ምርኮኞቻችሁን አንጹ።

20. ማናቸውንም ልብስ እንዲሁም ከቈዳ፣ ከፍየል ጠጒር ወይም ከዕንጨት የተሠራ ማንኛውንም ነገር አንጹ።”

21. ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ወደ ጦርነት ሄደው የነበሩትን ወታደሮች እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የሰጠው የሕጉ ሥርዐት ይህ ነው፤

22. ወርቅ፣ ብር፣ ናስ፣ ብረት፣ ቈርቈሮ፣ እርሳስ

23. እንዲሁም እሳትን መቋቋም የሚችል ማንኛውም ነገር በእሳት ውስጥ ማለፍ አለበት፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል፤ ይህም ሆኖ መንጻት አለበት። እሳትን መቋቋም የማይችል ማንኛውም ነገር በዚሁ ውሃ ውስጥ ማለፍ አለበት።

24. በሰባተኛው ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፤ ትነጻላችሁም፤ ከዚያም ወደ ሰፈር መግባት ትችላላችሁ።”

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

26. “አንተ፣ ካህኑ አልዓዛርና በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያሉት የየቤተ ሰቡ አለቆች ሆናችሁ የተማረከውን ሕዝብና እንስሳት ሁሉ ቊጠሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 31