ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 22:4-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሞዓባውያንም የምድያምን ሽማግሌዎች፣ “በሬ የመስክ ሣር ጠራርጎ እንደሚበላ ሁሉ፣ ይህም ሰራዊት በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሏቸው።ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፣

5. ከወንዙ ዳር ባለች በትውልድ አገሩ በምትገኝ በፋቱራ የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እንዲጠሩት መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤እነሆ ከብዛቱ የተነሣ ምድሩን የሸፈነ ሕዝብ ከግብፅ ወጥቶ በአቅራቢያዬ ሰፍሮአል።

6. ስለዚህ ይህን ሕዝብ መቋቋም ስለማልችል መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባትም ድል አድርጌ ከአገሪቱ ላስወጣቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ አንተ የምትባርከው ቡሩክ፣ የምትረግመውም ርጉም እንደሚሆን ዐውቃለሁና።”

7. የሞዓብና የምድያም ሽማግሌዎችም ለሟርት የሚከፈለውን ዋጋ ይዘው ሄዱ፤ በለዓም ዘንድ በደረሱ ጊዜም የባላቅን መልእክት ነገሩት።

8. በለዓምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጠኝን መልስ አመጣላችኋለሁና የዛሬን ሌሊት እዚሁ ዕደሩ” አላቸው። ስለዚህም የሞዓብ አለቆች ከእርሱ ዘንድ ቈዩ።

9. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “ከአንተ ጋር ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው።

10. በለዓምም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንዲህ አለው፤ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን መልእክት ልኮብኛል፤

11. ‘ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድሩን ገጽ አጥለቅልቆታል፤ ስለዚህ መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባት ልዋጋቸውና ላባርራቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል።’ ”

12. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን በለዓምን፣ “አብረሃቸው አትሂድ፤ የተባረከ ሕዝብ ስለ ሆነም አትርገመው” አለው።

13. በማግሥቱ ጠዋት በለዓም ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፣ “አብሬአችሁ እንዳልሄድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከልክሎኛልና እናንተ ወደ አገራችሁ ተመለሱ አላቸው።”

14. ስለዚህ የሞዓብ አለቆች ወደ ባላቅ ተመልሰው፣ “በለዓም አብሮን ለመምጣት እምቢ አለን” አሉት።

15. ከዚያም ባላቅ ከፊተኞቹ ይልቅ ቍጥራቸው የበዛና ይበልጥ የተከበሩ ሌሎች አለቆች ላከ።

16. እነርሱም ወደ በለዓም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን እንድንነግርህ ልኮናል፤ ወደ እኔ ለመምጣት የሚያግድህ ምንም ነገር አይኑር፤

17. ወሮታህን በእጅጉ እከፍላለሁ፤ የምትለውንም ሁሉ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።”

18. በለዓም ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ የአምላኬን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በመጣስ ከዚያ ያለፈ ወይም ያነሰ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አልችልም።

19. አሁንም ሌሎቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እናንተም ዛሬ እዚሁ ዕደሩና እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን እንደሚለኝ ደግሞ ልወቅ።”

20. በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች የመጡት እንድትሄድላቸው እስከ ሆነ ድረስ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 22