ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 22:29-41 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. በለዓምም መልሶ አህያዪቱን፣ “ስላላገጥሽብኝ ነዋ! በእጄ ሰይፍ ይዤ ቢሆን ኖሮ አሁኑኑ በገደልሁሽ ነበር” አላት።

30. አህያዪቱም ደግሞ በለዓምን እንዲህ አለችው፣ “ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተቀመጥክብኝ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ይህን የመሰለ ነገር የማድረግ ልማድ ነበረኝ?”እርሱም፣ “በጭራሽ!” አላት።

31. በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የበለዓምን ዐይን ከፈተ፤ እርሱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ እንደ ያዘ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ፤ ጐንበስ ብሎም በግንባሩ ተደፋ።

32. የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ስለ ምንድ ነው? መንገድህ በፊቴ ጠማማ ስለ ሆነ ልቃወምህ መጥቻለሁ።

33. አህያዪቱ አይታኝ ሦስቱንም ጊዜ ከፊቴ ዞር ባትልማ ኖሮ በእውነት እስካሁን አንተን በገደልሁህ አህያዪቱን ግን በሕይወት በተውኳት ነበር።

34. በለዓምም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ እኔን ለመቃወም መንገዱ ላይ መቆምህን አላወቅሁም፤ አሁንም ደስ የማትሰኝ ከሆነ እመለሳለሁ” አለው።

35. የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ በለዓምን፣ “መሄዱን ከሰዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው። ስለዚህ በለዓም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ።

36. በለዓም በመምጣት ላይ መሆኑን ባላቅ በሰማ ጊዜ በግዛቱ ዳርቻ በአርኖን ወሰን ላይ ወደምትገኘው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊቀበለው ወጣ።

37. ባላቅ በለዓምን፣ “በቶሎ እንድትመጣ ልኬብህ አልነበረምን? ለምን አልመጣህም? በርግጥ ወሮታህን ልከፍል የማልችል ሆኜ ነውን?” አለው።

38. በለዓምም፣ “ይኸው አሁን መጥቻለሁ፤ ግን እንዲያው ማንኛውንም ነገር መናገር እችላለሁን? እኔ መናገር የሚገባኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በአፌ ያስቀመጠውን ብቻ ነው” ብሎ መለሰለት።

39. ከዚያም በለዓም ከባላቅ ጋር ወደ ቂርያት ሐጾት ሄደ።

40. ባላቅም ከብቶችና በጎች ሠዋ፤ ከፊሉንም ለበለዓምና ከእርሱ ጋር ለነበሩት አለቆች ሰጣቸው።

41. በማግስቱ ጠዋት ባላቅ በለዓምን ወደ ባሞት በኣል አወጣው፤ እዚያም ሆኖ ሕዝብ በከፊል አየ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 22