ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 22:16-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እነርሱም ወደ በለዓም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን እንድንነግርህ ልኮናል፤ ወደ እኔ ለመምጣት የሚያግድህ ምንም ነገር አይኑር፤

17. ወሮታህን በእጅጉ እከፍላለሁ፤ የምትለውንም ሁሉ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።”

18. በለዓም ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ የአምላኬን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በመጣስ ከዚያ ያለፈ ወይም ያነሰ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አልችልም።

19. አሁንም ሌሎቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እናንተም ዛሬ እዚሁ ዕደሩና እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን እንደሚለኝ ደግሞ ልወቅ።”

20. በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች የመጡት እንድትሄድላቸው እስከ ሆነ ድረስ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ።”

21. በለዓም በጠዋት ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ።

22. ይሁን እንጂ በለዓም በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በጣም ተቈጥቶ ስለ ነበር የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ሊቃወመው በመንገዱ ላይ ቆመ። በለዓምም በአህያው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት አሽከሮቹም አብረው ነበሩ።

23. አህያዪቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በመንገድ ላይ መቆሙን ባየች ጊዜ ከመንገድ ወጥታ ዕርሻ ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገዱ እንድትመለስ መታት።

24. ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በሁለቱም በኩል ግንብ ባለበት በሁለት የወይን ተክል ቦታ መካከል በሚገኝ ጠባብ መተላለፊያ ላይ ቆመ።

25. አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር አጣበቀችው፤ ስለዚህም እንደ ገና መታት።

26. የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ ወደ ፊት ሄድ ብሎ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ።

27. አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ከበለዓም በታች ተኛች፤ በለዓም ተቈጥቶ ነበርና በበትሩ ደበደባት።

28. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የአህያዪቱን አፍ ከፈተ፤ በለዓምንም፣ “እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 22