ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 21:2-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. በዚያን ጊዜ እስራኤል፣ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ከሰጠኸን ከተሞቻቸውን ፈጽሞ እንደመስሳለን” ሲል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ተሳለ።

3. እግዚአብሔርም (ያህዌ) የእስራኤልን ልመና ሰምቶ ከነዓናውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰዎቹንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ከዚህ የተነሣም ስፍራው ሖርማ ተባለ።

4. እስራኤላውያን በኤዶም ዞረው ለመሄድ ስላሰቡ ከሖር ተራራ ተነሥተው ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ ተጓዙ፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በመንገድ ሳለ ትዕግሥቱ አለቀ፤

5. በእግዚአብሔርና (ኤሎሂም) በሙሴም ላይ ተነሥተው፣ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድ ነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ! ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” ሲሉ ተናገሩ።

6. በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) መርዘኛ እባቦች ሰደደባቸው፤ ሕዝቡን ነደፉ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሞቱ።

7. ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥቶ፣ “በእግዚአብሔርና (ያህዌ) በአንተ ላይ በመናገራችን በድለናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልይልን” አለ፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ።

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እባብ ሠርተህ በዕንጨት ላይ ስቀለው፤ የተነደፈውም ሁሉ ወደ እርሱ በማየት ይድናል” አለው፤

9. ስለዚህ ሙሴ የናስ እባብ ሠርቶ በዕንጨት ላይ ሰቀለ፤ ከዚያም በእባብ የተነደፈ ማናቸውም ሰው ወደ ናሱ እባብ በተመለከተ ጊዜ ይድን ነበር።

10. እስራኤላውያን ተጓዙ፤ በኦቦትም ሰፈሩ፤

11. ከዚያም ከኦቦት ተነሥተው፣ በፀሓይ መውጫ ትይዩ ባለው ምድረ በዳ በዒዮዓባሪም ሰፈሩ።

12. ከዚያም ተጒዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ።

13. ከዚያም ተነሥተው እስከ አሞራውያን ግዛት በሚዘልቀው ምድረ በዳ ባለው በአርኖን አጠገብ ሰፈሩ፤ አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል የሚገኝ የሞዓብ ወሰን ነው።

14. እንግዲህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በዚሁ የተነሣ ነው፤“ … በሱፋ ውስጥ የሚገኘው ዋሄብአርኖንና

15. ወደ ዔር የሚወስዱትበሞዓብ ድንበርም የሚገኙትየሸለቆች ተረተሮች።”

16. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ፣ “ሰዎቹን በአንድነት ሰብስባቸውና ውሃ እሰጣቸዋለሁ” ወዳለበት ብኤር ወደተባለው የውሃ ጒድጓድ ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

17. ከዚያም እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ፤“አንተ ምንጭ ሆይ ፍለቅ!እናንተም ዘምሩለት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 21