ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 20:19-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. እስራኤላውያንም መልሰው፣“አውራውን መንገድ ይዘን እንሄዳለን፤ እኛም ሆንን ከብቶቻችን የትኛውንም ውሃችሁን ከጠጣን ዋጋውን እንከፍላለን፤ በእግር አልፈን መሄድ ብቻ እንጂ ሌላ ምንም አንፈልግም።” አሏቸው።

20. ኤዶምም እንደ ገና፣“በዚህ ማለፍ አትችሉም።” የሚል መልስ ሰጣቸው።ከዚያም ኤዶም ብዙና ኀይለኛ የሆነ ሰራዊት አሰልፎ ሊወጋቸው ወጣ፤

21. ስለዚህ ኤዶም በግዛቱ አልፈው እንዳይሄዱ ስለ ከለከላቸው እስራኤላውያን ተመለሱ።

22. መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ከቃዴስ ተነሥቶ ወደ ሖር ተራራ መጣ።

23. እግዚአብሔርም (ያህዌ) በኤዶም ወሰን አጠገብ ባለው በሖር ተራራ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

24. “አሮን ወደ ወገኖቹ ይሰበሰባል፤ ሁለታችሁም በመሪባ ውሃ በትእዛዜ ላይ ዐምፃችኋልና ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ምድር አይገባም።

25. አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ወደ ሖር ተራራ ይዘሃቸው ውጣ።

26. አሮን ወደ ወገኖቹ ስለሚሰበሰብ ልብሱን አውልቀህ ልጁን አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም እዚያው ይሞታል።”

27. ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ መላው ማኅበረሰብ እያያቸው ወደ ሖር ተራራ ወጡ።

28. ሙሴም የአሮንን ልብስ አውልቆ ልጁን አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም እዚያው ተራራው ጫፍ ላይ ሞተ። ከዚያም ሙሴና አልዓዛር ከተራራው ወረዱ፤

29. መላው ማኅበረ ሰብም አሮን መሞቱን በተረዳ ጊዜ፣ የእስራኤል ቤት በሙሉ ሠላሳ ቀን አለቀሰለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 20