ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 20:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ወደ ጺን ምድረ በዳ መጥተው በቃዴስ ተቀመጡ፤ እዚያ ማርያም ሞተች፤ ተቀበረችም።

2. በዚህ ጊዜ ለማኅበረ ሰቡ የሚሆን ውሃ አልነበረም፤ ሕዝቡም ሙሴንና አሮንን በመቃወም ተሰበሰቡ።

3. ሙሴን ተጣሉት፤ እንዲህም አሉት፤ “ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በሞቱ ጊዜ ምነው እኛም ያኔ ሞተን ባረፍነው ኖሮ!

4. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማኅበረሰብ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድ ነው! ከነከብቶቻችን እዚሁ እንድናልቅ ነውን?

5. ከግብፅ አውጥታችሁ እህል ወይም በለስ፣ ወይን ወይም ሮማን ወደሌለበት ወደዚህ ክፉ ቦታ ያመጣችሁንስ ለምንድ ነው? የሚጠጣ ውሃ እንኳ ይታጣ!”

6. ሙሴና አሮን ከማኅበረ ሰቡ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው በግንባራቸው ተደፉ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ተገለጠላቸው።

7. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

8. “በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብሰቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል። አንተም ለማኅበረ ሰቡ ከዐለቱ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እነርሱና ከብቶቻቸውም ይጠጣሉ።”

9. ስለዚህም ሙሴ ልክ እንደታዘዘው በትሩን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወሰደ።

10. እርሱና አሮንም ማኅበሩን በዐለቱ ፊት አንድ ላይ ሰበሰቡ፤ ሙሴም፣ “እናንት ዐመፀኞች አድምጡ፤ ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” አላቸው።

11. ከዚያም ሙሴ እጁን ዘርግቶ በበትሩ ዐለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ውሃውም ተንዶለዶለ፤ ማኅበረ ሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ።

12. ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን፣ “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረሰብ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” አላቸው።

13. እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር የተጣሉበት፣ እርሱም ቅዱስ መሆኑን በመካከላቸው የገለጠበት ይህ የመሪባ ውሃ ነበር።

14. ሙሴ ከቃዴስ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤“ወንድምህ እስራኤል የሚለው ይህ ነው፤ የደረሰብን መከራ ሁሉ ምን እንደሆነ አንተም ታውቃለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 20