ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 16:41-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

41. በማግሥቱም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ፣ “እናንተ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ አጒረመረሙ።

42. ማኅበሩም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን ዘወር ሲሉ ደመና ድንኳኑን በድንገት ሸፍኖት አዩ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ተገለጠ።

43. ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ሄዱ።

44. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

45. “በቅጽበት አጠፋቸዋለሁና ከዚህ ማኅበር ራቅ” እነርሱም በግንባራቸው ተደፉ።

46. ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ቊጣ ወጥቶ መቅሠፍት ጀምሮአልና ጥናውን ወስደህ ዕጣን በመጨመር ከመሠዊያው እሳት አድርግበት፤ ፈጥነህም ወደ ማኅበሩ ሄደህ አስተሰርይላቸው” አለው።

47. ስለዚህ አሮን፣ ሙሴ በነገረው መሠረት ወደ ማኅበሩ መካከል ሮጦ ገባ፤ መቅሠፍቱም ቀደም ብሎ በሕዝቡ መካከል መስፋፋት ጀምሮ ነበር፤ ሆኖም አሮን ዕጣኑን ዐጥኖ አስተሰረየላቸው።

48. እርሱም በሕይወት ባሉትና በሞቱት መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።

49. ይሁን እንጂ በቆሬ ምክንያት የሞቱትን ሳይጨምር ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች ተቀሥፈው ሞቱ።

50. ከዚያም መቅሠፍቱ ቆመ፤ አሮንም ሙሴ ወዳለበት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 16