ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 14:2-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጒረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሉአቸው፤ “ምነው በግብፅ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ!

3. እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደዚች ምድር የሚያመጣን ለምንድ ነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ታዲያ ወደ ግብፅ መመለሱ አይሻለንም?”

4. እርስ በርሳቸውም፣ “አለቃ መርጠን ወደ ግብፅ እንመለስ” ተባባሉ።

5. ከዚያም ሙሴና አሮን እዚያ በተሰበሰቡት በመላው እስራኤላውያን ማኅበር ፊት በግንባራቸው ተደፉ።

6. ምድሪቱን ከሰለሏት መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዩፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤

7. ለመላው የእስራኤል ማኅበርም እንዲህ አሉ፤ “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት።

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) በእኛ ደስ ከተሰኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል።

9. ብቻ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩአቸው። ጥላቸው ተገፎአል፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከእኛ ጋር ነውና አትፍሯቸው።”

10. መላው ማኅበር ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነጋገሩ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በመገናኛው ድንኳን ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ።

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል” እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው?

12. በቸነፈር እመታዋለሁ፤ እደመስሰዋለሁም፤ አንተን ግን ብርቱና ታላቅ ለሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

13. ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብፃውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤

14. የተደረገውንም በዚች ምድር ለሚኖሩት ሰዎች ይነግሯቸዋል። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፣ አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር መሆንህን፣ ደግሞም አንተ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ፊት ለፊት እንደታየህና ደመናህ በላያቸው እንደሆነ፣ አንተም ቀን በደመና ዐምድ ሌሊትም በእሳት ዐምድ እፊት እፊታቸው እየሄድህ እንደ መራሃቸው ቀድሞውኑ ሰምተዋል።

15. ታዲያ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ብትፈጀው ዝናህን የሰሙ ሕዝቦች፣

16. ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው’ ይሉሃል።

17. “አሁንም እንዲህ ስትል በተናገርኸው መሠረት የጌታ ኀይል ይገለጥ፤

18. ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’

19. ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።”

20. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤

21. ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 14