ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 11:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል።

18. “ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ነገ ሥጋ ትበላላችሁና ራሳችሁን በመቀደስ ተዘጋጁ። “በግብፅ ተመችቶን ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ ማን ይሰጠናል!” ብላችሁ ያለቀሳችሁትን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰምቶአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ።

19. የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለአምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤

20. ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ፤ በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ንቃችሁ በፊቱ፣ “ለምን ከግብፅ ወጣን?” ብላችሁ አልቅሳችኋልና።’ ”

21. ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እነሆ እኔ በስድስት መቶ ሺህ እግረኛ መካከል እገኛለሁ፤ አንተ ደግሞ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ ብለሃል፤

22. ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?”

23. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክንድ ይህን ያህል አጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት።

24. ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው።

25. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም።

26. ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ።

27. አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 11