ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 8:20-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ።

21. ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።

22. ሙሴ ለቅድስና የሚሆነውን ሌላ አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በበጉ ራስ ላይ ጫኑ።

23. ሙሴ አውራ በጉን ዐረደ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት አስነካ፤

24. የአሮንንም ልጆች ወደ ፊት ጠራ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣትና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት አስነካ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ።

25. ሥቡን፣ ላቱን፣ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጒበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና ሥባቸውን እንዲሁም ቀኝ ወርቹን ወሰደ፤

26. በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ካለው፣ ያለ እርሾ የተጋገረ ዳቦ ካለበት መሶብ ላይ አንድ ኅብስት፣ አንድ በዘይት የተጋገረ ዳቦ እንዲሁም ስስ ቂጣ ወስዶ በሥቦቹና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖረ።

27. እነዚህንም ሁሉ ለአሮንና ለልጆቹ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱም የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዘወዙት።

28. ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው።

29. ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት፣ ድርሻው የሆነውን ክህነት የመስጫውን አውራ በግ ፍርምባ ወስዶ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዘወዘው።

30. ቀጥሎም ሙሴ በመቅቢያው ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት ወስዶ፣ በአሮንና በልብሱ እንዲሁም በአሮን ልጆችና በልብሳቸው ላይ ረጨ፤ በዚህም ሁኔታ አሮንንና ልብሱን፣ ልጆቹንና ልብሳቸውን ቀደሰ።

31. ሙሴም አሮንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉት፤ በዚያም፣ ‘አሮንና ልጆቹ ይብሉት’ ተብዬ በታዘዝሁት መሠረት፣ በክህነት መስጫው መሥዋዕት መሶብ ውስጥ ካለው ኅብስት ጋር ብሉት፤

32. የተረፈውንም ሥጋና ኅብስት በእሳት አቃጥሉ።

33. የክህነት መቀበያችሁ ሥርዐት እስከሚፈጸምበት እስከ ሰባት ቀን ድረስ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆዩ፤ ሥርዐቱንም ለመፈጸም ሰባት ቀን ይወስዳልና።

34. ዛሬ የተፈጸመው ይህ ሥርዐት ለእናንተ ማስተሰረያ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ነው።

35. እንዳትሞቱ ሰባቱን ቀንና ሌሊት ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትለዩ፤ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) ሥርዐት ጠብቁ፤ የታዘዝሁት እንዲህ ነውና።”

36. አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 8