ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ ‘አንድ ሰው ስላየውና ስለሚያውቀው ነገር ሕጋዊ ምስክርነቱን እንዲሰጥ ተጠይቆ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆን፣ ይህ ሰው ኀጢአት ሠርቶአልና ይጠየቅበታል።

2. “ ‘ማንኛውም ሰው ሳያውቅ በሥርዐቱ መሠረት የተከለከለውን ርኩስ ነገር ቢነካ፣ ይኸውም፦ የረከሰ የአውሬ በድን ወይም የረከሰ የቤት እንስሳ በድን ወይም በደረቱ እየተሳበ የሚንቀሳቀሰውን የረከሰ ፍጥረት በድን ቢነካ ይህ ሰው ረክሶአል፤ በደለኛም ነው።

3. “ ‘ወይም የሰውን ርኵሰት ይኸውም ርኵስ የሚያደርገውን ማናቸውንም ነገር ሳያውቅ ቢነካ፣ ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል።

4. “ ‘ሰዎች በሚምሉበት በማናቸውም ነገር፣ በጎ ወይም ክፉ ለማድረግ ሳያስብ በግዴለሽነት ቢምል በኋላ ግን ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል።

5. “ ‘ማንኛውም ሰው ከእነዚህ በአንዱ በደለኛ ሆኖ ቢገኝ፣ የትኛውን ኀጢአት እንደሠራ ገልጾ መናዘዝ አለበት፤

6. ስለ ኀጢአቱም ቅጣት የኀጢአት መሥዋዕት እንድትሆነው ከመንጋው አንዲት የበግ ወይም የፍየል እንስት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ፤ ካህኑም ስለ ኀጢአቱ ያስተሰረይለታል።

7. “ ‘ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በግ ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች የመጀመሪያውን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ።

8. ወደ ካህኑም ያምጣቸው፤ እርሱም ለኀጢአት መሥዋዕት የምትሆነውን አስቀድሞ ያቅርብ፤ ራሷን ዐንገቷ ላይ ይቈልምም፤ ነገር ግን ቈርጦ አይጣል፤

9. ከኀጢአት መሥዋዕቱም ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ላይ ይርጨው፤ የተረፈውም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ይፍሰስ፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው።

10. ካህኑም ቀደም ሲል በታዘዘው መሠረት ሁለተኛዋን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ ካህኑም የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።

11. “ ‘ሰውየው ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ነገር ግን የኀጢአት መሥዋዕት ስለ ሆነ ዘይት አያፍስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት፤

12. ከዚያም ለካህኑ ያቅርብ፤ ካህኑም ለመታሰቢያ እንዲሆን ዕፍኝ ሙሉ ይዝገንለት፤ በእሳት ከሚቀርበውም ቊርባን በላይ አድርጎ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በመሠዊያው ላይ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው።

13. ሰውየው ከእነዚህ በአንዱ ኀጢአት ቢሠራ፣ ካህኑ በዚህ ሁኔታ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። ከመሥዋዕቱ የተረፈውም እንደ እህል ቊርባን ሁሉ ለካህኑ ይሆናል።’ ”

የበደል መሥዋዕት

14. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

15. “ማንኛውም ሰው በደል ቢፈጽም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከተቀደሰ ከማናቸውም ነገር በማጒደል ኀጢአት ቢሠራ፣ ከመንጋው እንከን የሌለበትን አውራ በግ የበደል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ። የዋጋውም ግምት በቤተ መቅደሱ ሰቅል መሠረት ተመዝኖ በጥሬ ብር ይሁን፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው።

16. ከተቀደሱ ነገሮች ያጐደለውንም ይተካ፤ የዚህንም ተመን አንድ አምስተኛ በላዩ ጨምሮ ለካህኑ ይስጥ፤ ካህኑም ከበጉ ጋር የበደል መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።

17. “ ‘ማንኛውም ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዛት ሳያውቅ አንዱን ተላልፎ ቢገኝ በደለኛ ነው፤ በኀጢአቱም ይጠየቅበታል።

18. እርሱም ከመንጋው ለበደል መሥዋዕት የሚሆን እንከን የሌለበት አውራ በግ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ዋጋውም ተመጣጣኝ ይሁን። ካህኑም በዚህ ሁኔታ ሰውየው ሳያውቅ ስለ ፈጸመው ስሕተት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።

19. ይህ የበደል መሥዋዕት ነው። ሰውየውም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ጥፋት በመፈጸሙ በደለኛ ነው።”