ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 4:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ካህኑ ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያለውንና ሽታው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ። የተረፈውን የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍሰው፤

8. ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ይኸውም፦ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብና ከሆድ ዕቃው ጋር የተያያዘውን ሥብ፣

9. ሁለቱንም ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጒበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋር አብሮ አውጥቶ ያቅርብ፤

10. ለኅብረት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንዳወጣ ሁሉ ሥቡን ያውጣ፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው።

11. ነገር ግን የወይፈኑን ቈዳና ሥጋውን ሁሉ፣ ጭንቅላቱንና እግሮቹን፣ ሆድ ዕቃውንና ፈርሱን፣

12. የወይፈኑን ብልት ሁሉ ከሰፈር ውጭ ዐመድ ወደሚፈስበት በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነው ስፍራ ይውሰደው፤ በተቈለለው ዐመድ ላይ ዕንጨት አንድዶ ያቃጥለው።

13. “ ‘መላው የእስራኤል ሕዝብ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አታድርጉ ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) ካዘዘውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ ይህ ሕዝብ ጥፋቱ ባይታወቀውም በደለኛ ነው።

14. የሕዝቡ ጉባኤ ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን በመገናኛው ድንኳን ፊት ያቅርብ።

15. የሕዝቡም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫኑ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይታረድ።

16. የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ።

17. ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ በመጋረጃው ትይዩ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 4