ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 4:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. “ ‘መላው የእስራኤል ሕዝብ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አታድርጉ ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) ካዘዘውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ ይህ ሕዝብ ጥፋቱ ባይታወቀውም በደለኛ ነው።

14. የሕዝቡ ጉባኤ ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን በመገናኛው ድንኳን ፊት ያቅርብ።

15. የሕዝቡም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫኑ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይታረድ።

16. የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ።

17. ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ በመጋረጃው ትይዩ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው።

18. ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያለውን የመሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍሰው።

19. ከወይፈኑም ሥቡን ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤

20. ለኀጢአት መሥዋዕት ባቀረበው ወይፈን ላይ እንዳደረገው ሁሉ፣ በዚህኛውም ወይፈን ያድርግ፤ በዚህም መሠረት ካህኑ ስለ ሕዝቡ ያስተሰረያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ።

21. ወይፈኑንም ከሰፈር ውጭ ያውጣው፤ የመጀመሪያውን ወይፈን እንዳቃጠለው ሁሉ ይህኛውንም ያቃጥል፤ ይህም ስለ ሕዝቡ የሚቀርብ የኀጢአት መሥዋዕት ነው።

22. “ ‘አንድ የሕዝብ መሪ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አምላኩም እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው።

23. ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ።

24. እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 4