ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 3:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. የአሮንም ልጆች በመሠዊያው በሚነደው ዕንጨት ላይ ባለው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አድርገው ያቃጥሉት፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል።

6. “ ‘ከበግ ወይም ከፍየሉ መንጋ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት የሚያቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕት ወይም እንስት ያቅርብ።

7. መሥዋዕቱ የበግ ጠቦት ከሆነም፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያምጣው፤

8. በጠቦቱ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይረደው፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት።

9. ከኅብረት መሥዋዕቱ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ ቊርባን አድርጎ ያምጣ፤ ሥቡን፣ እስከ ጀርባ ዐጥንቱ ድረስ የተቈረጠ ላቱን በሙሉ፣ የሆድ ዕቃውን የሸፈነውን ሥብ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር የተያያዘውን ሥብ ሁሉ፣

10. ሁለቱን ኵላሊቶች፣ ኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጒበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋር አብሮ አውጥቶ ያቅርብ።

11. ካህኑም ይህን ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ የመብል ቊርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል።

12. “ ‘መሥዋዕቱ ፍየል ከሆነ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ፤

13. በራሱም ላይ እጁን ይጫንበት፤ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይረደው፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት።

14. ከሚያቀርበውም መሥዋዕት ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ ቊርባን አድርጎ ያቅርብ፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር የተያያዘውን ሥብ ሁሉ፣

15. ሁለቱን ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ፣ እንዲሁም የጒበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋር አብሮ አውጥቶ ያቅርብ።

16. ካህኑም ይህን ሁሉ በእሳት የሚቀርብና ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የመብል ቊርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ሥብ ሁሉ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።

17. “ ‘በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ፣ ሥብ ወይም ደም ከቶ አትብሉ፤ ይህ ለመጪው ትውልድ ሁሉ የተሰጠ የዘላለም ሥርዐት ነው።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 3