ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 26:40-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

40. “ ‘ነገር ግን ለእኔ ያልታመኑበትንና በእኔም ላይ ያመፁበትን የራሳቸውን ኀጢአትና የአባቶቻቸውን ኀጢአት ቢናዘዙ፣

41. ይኸውም፣ እኔ ጠላት እንድሆንባቸውና ወደ ጠላቶቻቸው ምድር እንድሰዳቸው ያደረገኝን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድና ስለ ኀጢአታቸው የሚገባውን ቅጣት ቢቀበሉ፣

42. በዚያ ጊዜ ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ኪዳኔን፣ ከይስሐቅም ጋር የገባሁትን ኪዳኔን፣ ደግሞም ከአብርሃም ጋር የገባሁትን ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባታለሁ።

43. ምድሪቱ እነርሱ ለቀዋት ስለ ሄዱ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱ በሌሉበት ጊዜም ባድማ ሆና በሰንበትዋ ትደሰታለች፤ ሕጌን በማቃለላቸውና ሥርዐቴን በመናቃቸው፣ የኀጢአታቸውን ቅጣት ይቀበላሉ።

44. በዚህ ሁሉ ግን ከእነርሱ ጋር የገባሁትን ኪዳኔን በማፍረስ፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ፈጽሜ እስካጠፋቸው ድረስ አልተዋቸውም፤ አልጸየፋቸውምም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

45. ስለ እነርሱም ስል፣ አምላካቸው (ኤሎሂም) እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”

46. እግዚአብሔር (ያህዌ) በራሱና በእስራኤላውያን መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ በኩል ያቆማቸው ሥርዐቶች፣ ሕጎችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 26