ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 25:42-55 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

42. እስራኤላውያን ከግብፅ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ።

43. በጭካኔ አትግዛቸው፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ።

44. “ ‘የሚኖሩህ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ፣ በዙሪያህ ካሉት አሕዛብ መካከል የገዛሃቸው ባሪያዎች ይሁኑ።

45. እንደዚሁም በመካከላችሁ ከሚኖሩት መጻተኞችና ከተወለዱት ወገናቸው ባሪያዎችን ግዙ፤ ንብረታችሁም ይሁኑ።

46. እነርሱንም እንደ ንብረት ለልጆቻችሁ አውርሷቸው፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ባሪያዎች ይሁኑአችሁ፤ እስራኤላውያን ወገኖቻችሁን ግን በጭካኔ አትግዟቸው።

47. “ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆንና ከወገናችሁ አንዱ ደኽይቶ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ወይም ከመጻተኛው ወገን ለአንዱ ራሱን ቢሸጥ፣

48. ከተሸጠ በኋላ ሊዋጅ ይችላል። ከዘመዶቹም አንዱ፦

49. አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ወይም ከወገኖቹ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ ይዋጀው፤ ሀብት ካገኘም ራሱን መዋጀት ይችላል።

50. እርሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንሥቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ከገዛው ሰው ጋር በመሆን ይቊጠር፤ ነጻ የሚለቀቅበትም ዋጋ በእነዚያ ዓመታት ለአንድ ቅጥር ሠራተኛ በሚከፈለው መሠረት ይተመናል።

51. ብዙ ዓመት የሚቀረው ከሆነም፣ እርሱን ለመግዛት ከተከፈለው ዋጋ ላይ በቀረው ዓመት መጠን ለሚዋጅበት መልስ ይክፈል።

52. እስከ ኢዮቤልዩ ድረስ የሚቀረው ጥቂት ዓመት ከሆነም፣ በቀረው ዓመት መጠን የሚዋጅበትን መልስ ይክፈል።

53. ከዓመት እስከ ዓመት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ይኑር፤ አሳዳሪውም በፊትህ በጭካኔ አይግዛው።

54. “ ‘ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ እንኳ መዋጀት ባይችል፣ እርሱና ልጆቹ በኢዮቤልዩ ዓመት በነጻ ይለቀቁ፤

55. እስራኤላውያን ለእኔ አገልጋዮቼ ናቸውና። እነርሱ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 25