ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 25:27-42 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

27. ርስቱን ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሽያጭ ዘመን በመቊጠር የዋጋውን ልዩነት ለገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ገዛ ርስቱ ይመለስ።

28. ነገር ግን ዋጋውን መመለስ ካልቻለ፣ የሸጠው ርስት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የገዢው ንብረት ሆኖ ይቈያል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ለባለቤቱ ይመለሳል፤ ሰውየውም ወደ ርስቱ ይመለሳል።

29. “ ‘ማንኛውም ሰው ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤቱን ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ሊዋጀው ይችላል፤ የመዋጀት መብቱ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ነው።

30. አንዱ ዓመት ከማለቁ በፊት መዋጀት ካልቻለ ግን፣ ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ ያለው ቤት የገዢውና የልጅ ልጆቹ ንብረት ሆኖ ይቀራል፤ በኢዮቤልዩ አይመለስለትም።

31. ቅጥር በዙሪያው ባልተሠራለት መንደር ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ግን እንደ ዕርሻ መሬት ተቈጥረው ሊዋጁ ይችላሉ፤ በኢዮቤልዩም ይመለሳሉ።

32. “ ‘ነገር ግን ሌዋውያን የራሳቸው በሆኑት ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን ቤቶቻቸውን ምንጊዜም የመዋጀት መብት አላቸው።

33. ሌዋውያን በከተማቸው ያለውን ቤታቸውን ቢሸጡና መዋጀት ባይችሉ፣ በኢዮቤልዩ ይመለሳል፤ በሌዋውያን ከተሞች የሚገኙ ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል የሌዋውያን ንብረት ናቸውና።

34. በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት ግን አይሸጥ፤ ለዘላለም ቋሚ ንብረታቸው ነውና።

35. “ ‘በመካከልህ ከወገንህ አንዱ ቢደኸይ፣ ራሱንም መርዳት ባይችል፣ በመካከልህ ይኖር ዘንድ መጻተኛውን ወይም እንግዳውን እንደ ምትረዳ እርዳው።

36. ወገንህ በመካከልህ ይኖር ዘንድ ምንም ዐይነት ወለድ አትቀበለው፤ አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራው።

37. ገንዘብህን በዐራጣ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት።

38. የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ (ኤሎሂም) ልሆን፣ ከግብፅ ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

39. “ ‘ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተም ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው።

40. በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቊጠረው፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ይሥራልህ፤

41. ከዚያም በኋላ እርሱና ልጆቹ በነጻ ይለቀቁ፤ ወደ ቤተ ሰቡና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለስ።

42. እስራኤላውያን ከግብፅ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 25