ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 25:21-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች።

22. በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ።

23. “ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ።

24. ርስት አድርጋችሁ በምትይዙት ምድር ሁሉ መሬት የሚዋጅበት ሁኔታ እንዲኖር አድርጉ።

25. “ ‘ከወገንህ አንዱ ደኽይቶ ርስቱን ቢሸጥ፣ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወገኑ የሸጠውን ይዋጅለት።

26. ነገር ግን ሰውየው ርስቱን የሚዋጅለት ምንም ዘመድ ባይኖረውና፣ እርሱ ራሱ መዋጀት የሚችልበትን ሀብት ቢያገኝ፣

27. ርስቱን ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሽያጭ ዘመን በመቊጠር የዋጋውን ልዩነት ለገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ገዛ ርስቱ ይመለስ።

28. ነገር ግን ዋጋውን መመለስ ካልቻለ፣ የሸጠው ርስት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የገዢው ንብረት ሆኖ ይቈያል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ለባለቤቱ ይመለሳል፤ ሰውየውም ወደ ርስቱ ይመለሳል።

29. “ ‘ማንኛውም ሰው ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤቱን ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ሊዋጀው ይችላል፤ የመዋጀት መብቱ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 25