ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የሚቀርብ ዘይትና ኅብስት

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2. “መብራቶቹ ያለ ማቋረጥ እንዲያበሩ ከወይራ ተጨምቆ የተጠለለ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው።

3. አሮንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ መጋረጃ ውጭ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያሉትን መብራቶች ከምሽት እስከ ንጋት ያለ ማቋረጥ ያሰናዳቸው፤ ይህም ለትውል ዶቻችሁ ሥርዐት ነው።

4. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ ያሉት መብራቶች ያለ ማቋረጥ መሰናዳት አለባቸው።

5. “የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ እያንዳንዱ ኅብስትም በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ይጋገር።

6. እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ረድፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ባለው የንጹሕ ወርቅ ጠረጴዛ ላይ አኑራቸው።

7. ከኅብስቱ ጋር የመታሰቢያ ድርሻ ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት እንዲሆን ንጹሕ ዕጣን በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ አኑር።

8. ኅብስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ይወክል ዘንድ ዘወትር በየሰንበቱ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይደርደር፤ ይህም የዘላለም ቃል ኪዳን ነው።

9. ኅብስቱ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ነው፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ድርሻቸው ነውና።”

እግዚአብሔርን መስደብ የሚያስከትለው ቅጣት

10. እናቱ እስራኤላዊት፣ አባቱ ግብፃዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጣ፤ በሰፈርም ውስጥ ከአንድ እስራኤላዊ ጋር ተጣሉ።

11. የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም በማቃለል ሰደበ፤ ስለዚህም ወደ ሙሴ አመጡት፤ የሰውየው እናት ስም ሰሎሚት ነበር፤ እርሷም ከዳን ወገን የተወለደው የደብራይ ልጅ ነበረች።

12. የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈቃድም ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት።

13. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

14. “ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ ሲሳደብ የሰሙት ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገረው።

15. እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው አምላኩን (ኤሎሂም) ቢሳደብ ኀጢአት ሠርቶአልና ይጠየቅበታል።

16. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም የሚሳደብ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ማኅበሩ ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ከሰደበ ይገደል።

17. “ ‘ሰውን ደብድቦ የገደለ ይገደል።

18. የሌላውን ሰው እንስሳ ደብድቦ የገደለ ማንኛውም ሰው ያንኑ ዐይነት እንስሳ ይተካለት።

19. ማንኛውም ሰው በባልንጀራው ላይ ጒዳት ቢያደርስ የዚያው ዐይነት ጒዳት ይፈጸምበት፤

20. ይኸውም በስብራት ፈንታ ስብራት፣ በዐይን ፈንታ ዐይን፣ በጥርስ ፈንታ ጥርስ ማለት ነው። በሌላው ሰው ላይ ያደረሰው ጒዳት በእርሱም ላይ ይድረስበት፤

21. እንስሳ የገደለ ማንኛውም ሰው በገደለው ፈንታ ይተካ፤ ሰው የገደለ ግን ይገደል።

22. ለመጻተኛው ሆነ ለአገር ተወላጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይኑራችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’ ”

23. ሙሴም ይህን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ እነርሱም ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወገሩት፤ እስራኤላውያንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።