ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 22:4-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. “ ‘ከአሮን ዘር ተላላፊ የቈዳ በሽታ ያለበት ወይም ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ማንኛውም ሰው እስኪነጻ ድረስ ቅዱሱን መሥዋዕት አይብላ፤ እንዲሁም በአስከሬን የረከሰውን ነገር ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበትን ሰው ቢነካ፣

5. ወይም በደረቱ የሚሳብ የሚያረክስ ነገርን ወይም የሚያረክስ ማንኛውንም ሰው ቢነካ፣ የቱንም ዐይነት ርኵሰት ቢሆን፣

6. እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።

7. ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ የተቀደሰውን መሥዋዕት መብላት ይችላል፤ ምግቡ ነውና።

8. እንዳይረክስ ማንኛውንም ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

9. “ ‘ካህናት ትእዛዛቴን በመናቅ በደለኛ እንዳይሆኑና እንዳይሞቱ ይጠብቋቸው፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

10. “ ‘ከካህን ቤተ ሰብ በቀር የካህኑ እንግዳም ሆነ ቅጥር ሠራተኛ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 22