ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 19:25-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. በአምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

26. “ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ፤“ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ።

27. “ ‘የራስ ጠጒራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቊረጡ።

28. “ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

29. “ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኵሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት።

30. “ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

31. “ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

32. “ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

33. “ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ አብሮአችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤

34. አብሮአችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

35. “ ‘በመስፈሪያ ወይም በሚዛን አታጭ በርብሩ።

36. እውነተኛ መለኪያ፣ እውነተኛ መመዘኛ፣ እውነተኛ የኢፍ መስፈሪያ፣ እውነተኛ የኢን መስፈሪያ ይኑራችሁ። ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

37. “ ‘ሥርዐቴንና ሕጌን ሁሉ ጠብቁ፤ ተከተሏቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 19