ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የስርየት ቀን

1. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በቀረቡ ጊዜ ከሞቱት፣ ከሁለቱ የአሮን ልጆች ሞት በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ተናገረው።

2. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው “እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመና ውስጥ እገለጣለሁና፣ ወንድምህ አሮን በመጋረጃው ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ማለት በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ፊት፣ በፈለገ ጊዜ ሁሉ እንዳይገባና እንዳይሞት ንገረው።

3. ወደ ተቀደሰው ስፍራ በሚገባበት ጊዜ፣ አሮን እንዲህ ያድርግ፦ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይዞ ይምጣ፤

4. የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፤ በሰውነቱ ላይ የሚያርፈውን ከበፍታ የተሠራውን የውስጥ ሱሪ ያጥልቅ፤ የበፍታውን መታጠቂያ ይታጠቅ፤ የበፍታውን መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ ልብሶቹ የተቀደሱ በመሆናቸው እነዚህን ከመልበሱ በፊት ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ።

5. ከእስራኤል ማኅበረሰብ ለኀጢአት መሥዋዕት ሁለት ተባዕት ፍየሎች፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ።

6. “አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ፣ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤

7. ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቁማቸው።

8. አሮንም አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ)፣ ሌላውን ለሚለቀቀው ፍየል ለማድረግ በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጣል።

9. በዕጣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የደረሰውንም ፍየል አምጥቶ ለኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ይሠዋ።

10. ወደ ምድረ በዳ ተለቅቆ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ፣ እንዲለቀቅ ዕጣ የወጣበትን ፍየል ከነሕይወቱ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ።

11. “አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤ ወይፈኑንም ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረድ።

12. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ካለው መሠዊያ ፍም ተወስዶ የተሞላበትን ጥና ይያዝ፤ ሁለት እጅ ሙሉ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን ይውሰድ፤ እነዚህንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ይዞ ይግባ።

13. እንዳይሞትም የዕጣኑ ጢስ በምስክሩ ላይ ያለውን ስርየት መክደኛ ይሸፍነው ዘንድ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ይጨምረው።

14. ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ፊተኛው ወገን ላይ በጣቱ ይርጭ፤ ደግሞም በስርየቱ መክደኛ ትይዩ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭ።

15. “ፍየሉንም ለሕዝቡ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረደው፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ወስዶ በወይፈኑ ደም እንዳደረገው በዚህኛው ያድርግ፤ ደሙን በስርየቱ መክደኛ ላይ፣ እንዲሁም በመክደኛው ትይዩ ይርጭ።

16. ከእስራኤላውያን ርኵሰትና ዐመፅ፣ ከየትኛውም ኀጢአታቸው ይነጻ ዘንድ በዚህ ሁኔታ ለቅድስተ ቅዱሳኑ ያስተሰርይለታል፤ በርኵሰታቸው መካከል በእነርሱ ዘንድ ላለችውም የመገናኛዋ ድንኳን እንደዚሁ ያደርጋል።

17. አሮን ለማስተሰረይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ አስተሰርዮ እስኪወጣ ድረስ ማንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አይገኝ።

18. “ከዚያም መጥቶ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዳለው መሠዊያ ይምጣ፤ ለመሠዊያውም ያስተሰርይለት፤ ከወይፈኑና ከፍየሉ ደም ወስዶ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ያስነካ፤

19. ከእስራኤላውያንም ርኵሰት መሠዊያውን ለማንጻትና ለመቀደስ ከደሙ ወስዶ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭበት።

20. “አሮን ለቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ለመገናኛው ድንኳንና ለመሠዊያው የሚያደርገውን ስርየት ከፈጸመ በኋላ በሕይወት ያለውን ፍየል ወደ ፊት ያቅርበው፤

21. ሁለት እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ በላዩም የእስራኤላውያንን ክፋትና ዐመፅ፣ ኀጢአታቸውን ሁሉ በሙሉ ይናዘዝበት፤ እነዚህንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ ፍየሉንም ለዚሁ ተግባር በተመደበ ሰው እጅ ወደ ምድረ በዳ ይስደደው።

22. ፍየሉም ኀጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፤ ሰውየውም ፍየሉን ሰው ሊኖርበት በማይችል ስፍራ ይልቀቀው።

23. “ከዚህ በኋላ አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ሄዶ፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ሊገባ ሲል የለበሳቸውን የበፍታ ልብሶች አውልቆ፣ በዚያው ይተዋቸው።

24. በተቀደሰውም ስፍራ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ የዘወትር ልብሱንም ይልበስ፤ ከዚያም ወጥቶ ለራሱ ማስተሰረያ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፣ ለሕዝቡም ማስተሰረያ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ።

25. የኀጢአት መሥዋዕቱንም በመሠዊያው ላይ ያቃጥል።

26. “የሚለቀቀውን ፍየል የወሰደው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል።

27. ደማቸው ለማስተሰረያነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የገባው፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የቀረቡት ወይፈንና ፍየል ከሰፈር ውጭ ተወስደው ቈዳቸው፣ ሥጋቸውና ፈርሳቸው ይቃጠል።

28. እነዚህንም የሚያቃጥል ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል።

29. “ለእናንተ የተሰጣችሁ የዘላለም ሥርዐት ይህ ነው፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ሰውነታችሁን አድክሙ፤ የአገሩ ተወላጅም ሆነ በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ምንም ሥራ አይሥራ፤

30. የምትነጹበት ስርየት በዚች ዕለት ይደረግላችኋልና በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ከኀጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ።

31. ይህች የፍጹም ዕረፍት ሰንበት ናት፤ ሰውነታችሁን አድክሙባት፤ የዘላለም ሥርዐት ናት።

32. ሊቀ ካህናት ለመሆን አባቱን በመተካት የተቀባና የተሾመ ካህን ያስተሰርይ፤ የተቀደሰውንም የበፍታ ልብስ ይልበስ፤

33. ለቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ለመገናኛው ድንኳንና ለመሠዊያው፣ ለካህናቱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ ያስተሰርይ።

34. “ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሁናችሁ፤ በዚህም ሥርዐት መሠረት ለእስራኤላውያን ኀጢአት ሁሉ በዓመት አንድ ጊዜ ስርየት ይደረግ።” እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ ተደረገ።