ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 14:19-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. “ካህኑም የኀጢአት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከርኵሰቱ ለሚነጻውም ሰው ያስተሰርይለት፤ ከዚህ በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ይረድ፤

20. ከእህል ቊርባኑም ጋር በመሠዊያው ላይ በማቅረብ ያስተሰርይለት፤ ሰውየውም ንጹሕ ይሆናል።

21. “ሰውየው ድኻ ከሆነና እነዚህን ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደለት፣ ማስተሰረያ እንዲሆነው የሚወዘወዝ አንድ ተባዕት የበግ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፣ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለእህል ቊርባን ያቅርብ፤ ደግሞም አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ፤

22. እንዲሁም ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ዐቅሙ የፈቀደውን አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ።

23. “እነዚህንም በስምንተኛው ቀን ስለ መንጻቱ ሥርዐት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ።

24. ካህኑም ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውን የበግ ጠቦትና አንድ ሎግ ዘይት ይቀበል፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዛቸው።

25. ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውንም የበግ ጠቦት ይረድ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮ ታችኛ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ፤

26. ከዘይቱም ጥቂቱን በግራ እጁ መዳፍ ውስጥ ያፍስስ፤

27. የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ ይርጭ።

28. በመዳፉ ከያዘው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የበደል መሥዋዕቱን ደም ባስነካበት ቦታ፣ ይኸውም የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ።

29. ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በመዳፉ ከያዘው ዘይት የቀረውን በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስ፤

30. ካህኑም ርግቦቹን ወይም የዋኖሶቹን ጫጩቶች የሰውየው ዐቅም የፈቀደውን ይሠዋል፤

31. ከእነዚህም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉ ቊርባን ጋር ያቅርብ፤ በዚህም ሁኔታ ካህኑ ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል።”

32. ተላላፊ የቈዳ በሽታ ይዞት የሚነጻበትን መደበኛ መሥዋዕት ለማቅረብ ዐቅም ላነሠው ሰው ሕጉ ይህ ነው።

33. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 14