ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 13:44-59 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

44. ሰውየው ደዌ አለበት፤ ርኵስም ነው፤ በራሱ ላይ ካለው ቊስል የተነሣም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ።

45. “እንዲህ ያለ ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የተቀደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጒሩን ይግለጥ፤ እስከ አፍንጫውም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ ርኩስ ነኝ’ እያለ ይጩኽ።

46. ተላላፊ በሽታው እስካለበት ጊዜ ድረስ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጥ፤ ከሰፈር ውጪም ይኑር።

47. “ከበግ ጠጒር ወይም ከበፍታ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት ልብስ በተላላፊ በሽታ ቢበከል፣

48. በሸማኔ ዕቃ ወይም በእጅ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት የበግ ጠጒር ወይም የበፍታ ልብስ፣ ወይም ማንኛውም ቈዳ ወይም ከቈዳ የተሠራ ነገር ቢሆን፣

49. በልብስ ወይም በዐጐዛ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራ ወይም በእጅ በተጠለፈ ወይም ከቈዳ በተሠራ ዕቃ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት፣ እየሰፋ የሚሄድ ተላላፊ በሽታ ስለ ሆነ ካህኑ ይየው።

50. ካህኑ ደዌውን ይመርምር፤ በደዌ የተበከለውንም ዕቃ ሰባት ቀን ያግልል።

51. በሰባተኛውም ቀን ይመርምረው፤ ደዌው በልብሱ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ወይም ለማናቸውም አገልግሎት በሚውል ዐጐዛ ላይ ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ ክፉ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው።

52. ልብሱን ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራውን ወይም በእጅ የተጠለፈውን የበግ ጠጒር ወይም በፍታ ወይም ደዌው ያለበትን ማንኛውንም ከቈዳ የተሠራ ዕቃ ያቃጥል፤ ደዌው ክፉ ነውና፤ ዕቃው ይቃጠል።

53. “ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ፣ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ተስፋፍቶ ካልተገኘ፣

54. ካህኑ ደዌው ያለበት ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ዕቃውንም ሰባት ቀን ደግሞ ያግልል።

55. ደዌው ያለበት ዕቃ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው ባይስፋፋም እንኳ መልኩን ካልለወጠ፣ ርኩስ ነው፤ ደዌው የወጣው በውስጥም ሆነ በውጭ ዕቃው በእሳት ይቃጠል።

56. ዕቃው ከታጠበ በኋላ ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው ከስሞ ቢገኝ፣ በደዌ የተበከለውን ቦታ ከልብሱ ወይም ከቈዳው ወይም በሸማኔ ዕቃ ከተሠራው ወይም በእጅ ከተጠለፈው ጨርቅ ቀዶ ያውጣ።

57. ነገር ግን ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ቢታይ፣ መስፋፋቱ ስለ ሆነ ደዌው ያለበት ማንኛውም ነገር በእሳት ይቃጠል።

58. ታጥቦ ከደዌ የጠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ እንደ ገና ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።”

59. ከበግ ጠጒር ወይም ከበፍታ የተሠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ በደዌ ቢበከል፣ ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለማወቅ ሕጉ ይህ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 13