ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 13:16-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ቀይ ሥጋ ተለውጦ ከነጣ ግን ወደ ካህኑ ይሂድ፤

17. ካህኑም ይመርምረው፤ ቊስሎች ወደ ነጭነት ተለውጠው ከተገኙ፣ የታመመው ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ንጹሕም ይሆናል።

18. “አንድ ሰው በገላው ላይ ዕባጭ ወጥቶ ቢድን፣

19. ዕባጩ በነበረበት ቦታ ላይም ነጭ ዕብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቍቻ ቢታይ፣ ካህኑ ዘንድ ይቅረብ።

20. ካህኑም ይመርምረው፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ የገባ ቢሆን በቦታውም ያለው ጠጒር ቢነጣ፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ።

21. ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጒር በውስጡ ከሌለ፣ ዘልቆ ካልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰባት ቀን ያግልለው።

22. በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ካገኘውም፣ ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚተላለፍ ነው።

23. ቋቍቻው ግን ባለበት ከቈየና ወደ ሌላ ስፍራ ካልተስፋፋ፣ የዕባጩ ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ።

24. “አንድ ሰው እሳት ቈዳውን ቢያቃጥለውና በተቃጠለው ስፍራ ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቍቻ ቢታይበት፣

25. ካህኑ ይመርምረው፤ ቋቍቻው ባለበትም ቦታ ያለው ጠጒር ቢነጣና ከቈዳው በታች ዘልቆ ቢገባ፣ በቃጠሎው ሰበብ ከውስጥ የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው፤ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።

26. ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጒር የሌለበት፣ ከቈዳውም በታች ዘልቆ ያልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው።

27. በሰባተኛው ቀን ካህኑ ይመርምረው፤ በሽታውም በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ቢያገኘው፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።

28. ቋቍቻ ባለበት ከቈየና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ይልቁንም እየከሰመ ከሄደ፣ በቃጠሎው ሰበብ የተከሠተ ዕብጠት ነውና ካህኑ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ የቃጠሎው ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም።

29. “በወንድ ወይም በሴት ዐናት ወይም አገጭ ላይ ቊስል ቢወጣ፣

30. ካህኑ ቊስሉን ይመርምር፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ ከገባ፣ በውስጡም ያለው ጠጒር ቢጫና ቀጭን ከሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚያሳክክ የራስ ወይም የአገጭ ተላላፊ በሽታ ነው።

31. ካህኑ እንዲህ ዐይነቱን ቊስል በሚመረምርበት ጊዜ፣ ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባና በውስጡም ጥቊር ጠጒር ከሌለ፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 13