ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 8:20-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. በተጨማሪም ዳዊትና ሹማምቱ ሌዋውያኑን እንዲረዳ ካቋቋሙት ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ቡድን 220 አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየስማቸው ተመዘገቡ።

21. ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጒዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ።

22. “መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቊጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር።

23. ስለዚህ ጾምን፤ ወደ አምላካችንም ስለዚህ ነገር ልመና አቀረብን፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ።

24. እኔም ከዋና ዋናዎቹ ካህናትም ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፣ ከእነርሱም ጋር ሰራብያን፣ ሐሸቢያንና ከወንድሞቻቸውም መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ፤

25. ንጉሡ፣ አማካሪዎቹ፣ ሹሞቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን ብር፣ ወርቅና ዕቃ ሁሉ መዝኜ ሰጠኋቸው።

26. ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብር፣ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፣ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፣

27. አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ ሃያ የወርቅ ወጭቶችና እንደ ወርቅ ነጥረው ከሚያብረቀርቅ ናስ የተሠሩ ሁለት ዕቃዎችን መዝኜ በእጃቸው አስረከብኋቸው።

28. እንዲህም አልኋቸው፤ “እናንተና እነዚህ ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ብሩና ወርቁ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር በበጎ ፈቃድ የቀረበ መባ ነው።

29. ኢየሩሳሌም በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤት ክፍሎች ውስጥ በዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ በሌዋውያኑና በየቤተ ሰቡ የእስራኤል አለቆች ፊት እስክትመዝኗቸው ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።”

30. ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ አምላካችን ቤት እንዲሄድ የተመዘነውን ብር፣ ወርቅና ንዋያተ ቅድሳት ተረከቡ።

31. እኛም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችን እጅ በላያችን ነበረች፤ እርሱም ከጠላቶቻችንና በመንገድ ላይ ከሚሸምቁ አዳነን።

32. ኢየሩሳሌምም ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ዐረፍን።

33. በአራተኛው ቀን ብሩን፣ ወርቁንና ንዋያተ ቅድሳቱን በአምላካችን ቤት መዝነን ለኦሪዮ ልጅ ለካህኑ ለሜሪሞት በእጁ አስረከብነው፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር፣ ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ።

34. ሁሉም ነገር ተቈጠረ፤ ተመዘነም፤ የተመዘነውም ሁሉ በዚያኑ ጊዜ ተመዘገበ።

35. ከዚያም ከምርኮ የተመለሱት፣ ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፣ ዘጠና ስድስት አውራ በጎችን፣ ሰባ ሰባት ተባዕት ጠቦቶችን፣ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ለእግዚአብሔር የቀረበ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበር።

36. የንጉሡንም ትእዛዝ ለንጉሡ እንደራሴዎችና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት አገረ ገዦች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት ረዱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 8