ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በባቢሎን ግምጃ ቤት የተቀመጡት መዛግብት እንዲመረመሩ ትእዛዝ ሰጠ።

2. በሜዶን አውራጃ በሚገኘው በአሕምታ ከተማ አንድ ጥቅልል ብራና ተገኘ፤ በውስጡም እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎበት ነበር፤ማስታወሻ፤

3. በንጉሥ ቂሮስ የመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም ስለሚገኘው የእግዚእብሔር ቤተ መቅደስ ንጉሡ የሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ቤተ መቅደሱ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ ሆኖ እንደ ገና ይሠራ፤ መሠረቱም ይጣል፤ ቁመቱ ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱም ሥልሳ ክንድ ይሁን፤

4. በሦስት ዙር ታላላቅ ድንጋዮችና በአንድ ዙር ዕንጨት ይሠራ፤ ወጪውም ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ይከፈል።

5. እንዲሁም ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች፣ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቦታቸው ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲመለሱ ይሁን፤ በእግዚአብሔርም ቤት ይቀመጡ።

6. አሁንም በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የሆንኸው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና እናንተም በዚያ አውራጃ የምትገኙ ተባባሪዎቻቸው ሁሉ ወደዚያ አትድረሱ።

7. በዚህም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ጣልቃ አትግቡ፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት የአይሁድ አገረ ገዥና የአይሁድ መሪዎች በቀድሞው ቦታ ላይ መልሰው ይሥሩት።

8. በተጨማሪም የአይሁድ መሪዎች ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና ሲሠሩ፣ እናንተ ምን እንደምታደርጉላቸው ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ሥራውም እንዳይቋረጥ የእነዚህ ሰዎች ወጪ በሙሉ ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከኤፍራጥስ ማዶ ከሚገኘው ገቢ ላይ ይከፈል።

9. ለሰማይ አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆን ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ነገር፣ ማለት ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ተባዕት ጠቦቶችን ስጧቸው፤ እንዲሁም ስንዴው፣ ጨዉ፣ የወይን ጠጁና ዘይቱ በኢየሩሳሌም ያሉት ካህናት በሚጠይቋችሁ መሠረት ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ይሰጣቸው።

10. ይህ የሚሆነው የሰማይ አምላክን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ ለንጉሡና ለወንድ ልጆቹም ደኅንነት እንዲጸልዩ ነው።

11. ደግሞም ይህን ትእዛዝ የሚለውጥ ማንም ሰው ቢኖር፣ ከቤቱ ምሰሶ ተነቅሎ በምሰሶው ላይ እንዲሰቀል፣ ስለ ወንጀሉም ቤቱ የቈሻሻ መጣያ እንዲሆን አዝዣለሁ።

12. ይህን ትእዛዝ ለማፍረስ ወይም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለማጥፋት እጁን የሚያነሣ ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ፣ ስሙን በዚያ እንዲኖር ያደረገ አምላክ ያጥፋው።እኔ ዳርዮስ በትጋት እንዲፈጸም ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 6