ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 3:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ኢያሱ፣ ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ፣ የዮሖዳያ ዘሮች ቀድምኤልና ወንዶች ልጆቹ፣ የኤንሐዳድ ወንዶች ልጆች፣ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው፣ ሌዋውያኑም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ሰዎች ለመቈጣጠር በአንድ ላይ ሆኑ።

10. ግንበኞቹ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት በጣሉ ጊዜ፣ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰውና መለከታቸውን ይዘው፣ ሌዋውያኑ የአሳፍ ልጆች ደግሞ ጸናጽል ይዘው፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት እግዚአብሔርን ለመወደስ ስፍራቸውን ያዙ።

11. በውዳሴና በምስጋናም ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲሉ ዘመሩ፤“ቸር ነውና፤ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።” የእግዚአብሔር ቤት መሠረት ስለ ተጣለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በታላቅ ድምፅ እልል እያሉ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ።

12. የቀድሞውን ቤተ መቅደስ ያዩ በዕድሜ የሸመገሉ ብዙ ካህናት፣ ሌዋውያንና የቤተ ሰብ አለቆች የዚህ ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል ባዩ ጊዜ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ሌሎቹ ግን የደስታ ጩኸት አሰሙ።

13. የሕዝቡ ጩኸት ድብልቅልቅ ያለ ስለ ነበር፣ የደስታውን እልልታ ከልቅሶው ጩኸት መለየት የሚችል ማንም አልነበረም፤ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 3