ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 10:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዕዝራ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ወድቆ በሚጸልይበት፣ በሚናዘዝበትና በሚያለቅስበት ጊዜ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የሚገኙበት እጅግ ብዙ የእስራኤል ማኅበር በዙሪያው ተሰበሰበ፤ እነርሱም እንደዚሁ አምርረው አለቀሱ።

2. ከዚያም ከኤላም ዘሮች አንዱ የሆነው የይሒኤል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ አለው፤ “በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ፣ ባዕዳን ሴቶችን በማግባታችን ለአምላካችን ታማኞች ሆነን አልተገኘንም፤ ይህም ሆኖ አሁንም ለእስራኤል ተስፋ አለ።

3. አሁንም እንደ ጌታዬ ምክርና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩ ሰዎች እነዚህን ሴቶችና ልጆቻቸውን ለመስደድ በአምላካችን ፊት ቃል ኪዳን እንግባ፤ በሕጉም መሠረት ይፈጸም።

4. ዕዝራ፣ ነገሩ በእጅህ ነው፤ ተነሥ! እኛም እንደግፍሃለን፤ በርትተህም፤ አድርገው።”

5. ዕዝራም ተነሥቶ ዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ ሌዋውያንና እስራኤል ሁሉ የቀረበውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ አስማላቸው፤ እነርሱም ማሉ።

6. ከዚያም ዕዝራ ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤልያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ክፍል ገባ፤ ምርኮኞቹ ታማኞች ሆነው ባለ መገኘታቸው ያለቅስ ነበር፤ በዚያም ምግብ አልቀመሰም፤ ውሃም አልጠጣም።

7. ከዚያም ምርኮኞቹ ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ፤

8. ዐዋጁም በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ማንም ሰው በሹማምቱና በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሠረት ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፣ ራሱም ከምርኮኞቹ ጉባኤ እንዲወገድ የሚያዝ ነበር።

9. ስለዚህ በሦስት ቀን ውስጥ የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ በዘጠነኛው ወር በሃያኛውም ቀን ሕዝቡ ሁሉ ስለ ወቅቱ ጒዳይና ስለ ከባዱ ዝናብ በመጨነቅ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀምጠው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 10