ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕንባቆም 2:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. “ታዲያ በእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ላይ በማፌዝና በመዘበት እንዲህ እያሉ ሁሉም አይሣለቁበትምን?“የተሰረቀውን ሸቀጥ ለራሱ ለሚያከማች፣ራሱን በዐመፅ ባለጠጋ ለሚያደርግ ወዮለት!ይህ የሚቀጥለውስ እስከ መቼ ነው?”

7. ባለ ዕዳ ያደረግሃቸው ድንገት አይነሡብህምን?ነቅተውስ አያስደነግጡህምን?በእጃቸውም ትወድቃለህ።

8. አንተ ብዙ ሕዝብ ስለ ዘረፍህ፣የተረፉት ሕዝቦች ይዘርፉሃል፤የሰው ደም አፍሰሃልና፤አገሮችንና ከተሞችን፣ በውስጣቸው የሚኖሩትን ሁሉ አጥፍተሃል።

9. “በተጭበረበረ ትርፍ መኖሪያውን ለሚገነባ፣ከጠላት እጅ ለማምለጥ፣ቤቱን በከፍታ ላይ ለሚሠራ ወዮለት!

10. የብዙ ሰዎች ነፍስ እንዲጠፋ አሢረሃል፤በገዛ ቤትህ ላይ ውርደትን፣ በራስህም ላይ ጥፋትን አምጥተሃል።

11. ድንጋይ ከቅጥሩ ውስጥ ይጮኻል፤ከዕንጨት የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይመልሱለታል።

12. “ከተማን ደም በማፍሰስ ለሚሠራ፣በወንጀልም ለሚመሠርታት ወዮለት።

13. ሰዎች ለእሳት ማገዶ እንዲሆን እንዲለፉ፣ሕዝቦችም በከንቱ እንዲደክሙ፣ እግዚአብሔር ጸባኦት ወስኖ የለምን?

14. ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን ሁሉ፣ምድርም የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና።

15. “ኀፍረተ ሥጋቸውን ለማየት፤ባልንጀሮቹን ለሚያጠጣ፣እስኪሰክሩም ድረስ ወይን ለሚቀዳላቸው ወዮለት!

16. በክብር ፈንታ ዕፍረት ትሞላለህ፤አሁን ደግሞ ተራው የአንተ ነውና፤ ጠጣ፤ ኀፍረተ ሥጋህም ይገለጥ፤ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ያለው ጽዋ ይመለስብሃል፤ክብርህንም ውርደት ይሸፍነዋል።

17. በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ያጥለቀልቅሃል፤እንስሳቱን ማጥፋትህም ያስደነግጥሃል፤የሰው ደም አፍሰሃልና፤አገሮችንና ከተሞችን በውስጣቸው የሚኖሩትንም ሁሉ አጥፍተሃልና።

18. “የሰው እጅ የቀረጸው ጣዖት፣ሐሰትንም የሚናገር ምስል ምን ፋይዳ አለው?ሠሪው በገዛ እጁ ሥራ ይታመናልና፣መናገር የማይችሉ ጣዖታትን ይሠራልና።

19. ዕንጨቱን፣ ‘ንቃ!’ሕይወት የሌለውንም ድንጋይ፣ ‘ተነሣ!’ ለሚል ወዮለት፤በውኑ ማስተማር ይችላልን?እነሆ፤ በወርቅና በብር ተለብጦአል፤እስትንፋስም የለውም።

20. እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፣ምድር ሁሉ በፊቱ ጸጥ ትበል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕንባቆም 2