ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕንባቆም 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ነቢዩ ዕንባቆም የተቀበለው ንግር፤

የዕንባቆም ማጒረምረም

2. እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?“ግፍ በዛ” ብዬ እየጮኽሁ፣አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው?

3. ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ?እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ?ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ጠብና ግጭት በዝቶአል።

4. ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፤ፍትሕ ድል አይነሣም፤ፍትሕ ይጣመም ዘንድ፣ክፉዎች ጻድቃንን ይከባሉ።

የእግዚአብሔር መልስ

5. “ቢነገራችሁም እንኳ፣የማታምኑትን እናንተን፣በዘመናችሁ አንድ ነገር ስለማደርግ፣እነሆ፤ ሕዝቡን እዩ፤ ተመልከቱም፤እጅግም ተደነቁ።

6. የራሳቸው ያልሆኑትን መኖሪያ ስፍራዎች ለመያዝ፣ምድርን ሁሉ የሚወሩትን፣ጨካኝና ፈጣን የሆኑትን፣ባቢሎናውያንን አስነሣለሁ።

7. እነርሱም የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ፍርዳቸውና ክብራቸው፣ከራሳቸው ይወጣል።

8. ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች፣ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው።ፈረሰኞቻቸው በፍጥነት ይጋልባሉ፤ከሩቅ ስፍራም ይመጣሉ።ነጥቆ ለመብላት እንደሚቸኵል አሞራ ይበራሉ፤

9. ሁሉም ለዐመፅ ታጥቀው ይመጣሉ።ሰራዊታቸው እንደ ምድረ በዳ ነፋስ ወደ ፊት ይገሠግሣል፤ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባል።

10. ነገሥታትን ይንቃል፤በገዦችም ላይ ያፌዛል፤በምሽግ ሁሉ ላይ ይሥቃል፤የዐፈር ቊልል ሠርቶም ይይዘዋል።

11. ከዚያም በኋላ እንደ ነፋስ ዐልፎ ይሄዳል፤ጒልበታቸውን አምላካቸው ያደረጉ በደለኞች ናቸው።

የዕንባቆም ዳግመኛ ማጒረምረም

12. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከዘላለም ጀምሮ ያለህ አይደለህምን?የእኔ አምላክ፣ የእኔ ቅዱስ እኛ አንሞትም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲፈርዱ ሾመሃቸዋል፤ዐለት ሆይ፤ ይቀጡ ዘንድ ሥልጣን ሰጠሃቸው።

13. ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤አንተ በደልን መታገሥ አትችልም፤ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትታገሣለህ?ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣ለምን ዝም ትላለህ?

14. አንተ ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣ገዥ እንደሌላቸውም የባሕር ፍጥረታት አደረግህ።

15. ክፉ ጠላት ሁሉንም በመንጠቆ ያወጣቸዋል፤በመረቡ ይይዛቸዋል፤በአሽክላው ውስጥ ይሰበስባቸዋል፤በዚህም ይደሰታል፤ ሐሤትም ያደርጋል።

16. በእነርሱ ተዝናንቶ ይኖራልና፤ምግቡም ሰብቶአል።ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፤ለአሽክላውም ያጥናል።