ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 51:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ፊት፣በበደል የተሞላች ብትሆንም፣እስራኤልንና ይሁዳን አምላካቸው፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር አልጣላቸውም።

6. “ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡፈጥናችሁም ሕይወታችሁን አትርፉ!በኀጢአቷ ምክንያት አትጥፉ። የእግዚአብሔር የበቀል ጊዜ ነው፤እርሱም የሥራዋን ይከፍላታል።

7. ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ የወርቅ ጽዋ ነበረች፤ምድርንም ሁሉ አሰከረች።ሕዝቦች ከወይን ጠጇ ጠጡ፤ስለዚህ አሁን አብደዋል።

8. ባቢሎን በድንገት ወድቃ ትሰበራለች፤ዋይ በሉላት!ምናልባት ልትፈወስ ስለምትችል፣ለቍስሏ የሚቀባ መድኀኒት ፈልጉላት።

9. “ ‘ባቢሎንን ለመፈወስ ሞክረን ነበር፤እርሷ ግን ልትፈወስ አትችልም፤ፍርዷ እስከ ሰማይ ስለ ደረሰ፣እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ስላለ፣ትተናት ወደየአገራችን እንሂድ።’

10. “ ‘እግዚአብሔር ቅንነታችንን መሰከረ፤ኑ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ያደረገውን፣በጽዮን እንናገር።’

11. “ፍላጾችን ሳሉ፤ጋሻዎችን አዘጋጁ፤ የእግዚአብሔር ሐሳብ ባቢሎንን ለማጥፋት ስለ ሆነ፣የሜዶንን ነገሥታት አነሣሥቶአል፤ እግዚአብሔር ይበቀላል፤ስለ ቤተ መቅደሱ ይበቀላል።

12. በባቢሎን ቅጥር ላይ ዐላማ አንሡጥበቃውን አጠናክሩ፤ዘብ ጠባቂዎችን አቁሙ፤ደፈጣ ተዋጊዎችን አዘጋጁ እግዚአብሔር በባቢሎን ሕዝብ ላይ የወሰነውን፣ዐላማውን ያከናውናል።

13. አንቺ በብዙ ውሃ አጠገብ የምትኖሪ፣በሀብትም የበለጸግሽ ሆይ፤የምትወገጂበት ጊዜ ወጥቶአል፤ፍጻሜሽ ደርሶአል።

14. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፤ብዛቱ እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ሰራዊት ያጥለቀልቅሻል፤እነርሱም በድል አድራጊነት በላይሽ ያቅራራሉ።

15. “ምድርን በኀይሉ የሠራ፣ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፣ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።

16. ድምፁን ባንጐደጐደ ጊዜ በሰማይ ውሆች ይናወጣሉ፤ጉሙን ከምድር ዳርቻ ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።

17. “እያንዳንዱ ሰው ጅልና ዕውቀት የለሽ ነው፤የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው በጣዖቱ ዐፍሮአል፤የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤እስትንፋስ የላቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 51