ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 51:15-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. “ምድርን በኀይሉ የሠራ፣ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፣ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።

16. ድምፁን ባንጐደጐደ ጊዜ በሰማይ ውሆች ይናወጣሉ፤ጉሙን ከምድር ዳርቻ ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።

17. “እያንዳንዱ ሰው ጅልና ዕውቀት የለሽ ነው፤የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው በጣዖቱ ዐፍሮአል፤የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤እስትንፋስ የላቸውም።

18. እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፣ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።

19. የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደ እነዚህ አይደለም፤እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

20. “አንቺ የእኔ ቈመጥ፣የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤በአንቺ ሕዝቦችን እሰባብራለሁ፤በአንቺ መንግሥታትን አጠፋለሁ፤

21. በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤በአንቺ ሠረገላውንና ሠረገላ ነጂውን እሰባብራለሁ፤

22. በአንቺ ወንዱንና ሴቱን እሰባብራለሁ፤በአንቺ ሽማግሌውንና ወጣቱን እሰባብራለሁ።በአንቺ ጐረምሳውንና ኰረዳዪቱን እሰባብራለሁ።

23. በአንቺ እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፣በአንቺ ገበሬውንና በሬውን እሰባብራለሁ፤በአንቺ ገዦችንና ባለ ሥልጣኖችን እሰባብራለሁ።

24. “በጽዮን ላይ ስላደረሱት ጥፋት ሁሉ ለባቢሎንና በባቢሎን ለሚኖሩት ሁሉ ዐይናችሁ እያየ ዋጋቸውን እከፍላቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

25. “አንቺ ምድርን ሁሉ ያጠፋሽ፣አጥፊ ተራራ ሆይ፤ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፣”ይላል እግዚአብሔር፤“እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ከገመገም ቍልቍል አንከባልልሻለሁ፤የተቃጠለም ተራራ አደርግሻለሁ።

26. ከአንቺ ለማእዘን የሚሆን ድንጋይ፣ለመሠረትም የሚሆን ዐለት አይወሰድም፤ለዘላለም ባድማ ትሆኛለሽ፤”ይላል እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 51