ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 48:4-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሞዓብ ትሰበራለች፤ልጆቿም ጩኸት ያሰማሉ።

5. ክፉኛ እያለቀሱ፣ወደ ሉሒት ሽቅብ ይወጣሉ፤ስለ ደረሰባቸውም ጥፋት መራራ ጩኸት እያሰሙ፣ወደ ሖርናይም ቍልቍል ይወርዳሉ።

6. ሽሹ፤ ሕይወታችሁንም አትርፉ!በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ሁኑ።

7. በድርጊታችሁና በብልጽግናችሁ ስለምትታመኑ፣እናንተም ትማረካላችሁ፣ካሞሽም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋር፣በምርኮ ይወሰዳል።

8. በእያንዳንዱ ከተማ ላይ አጥፊ ይመጣል፤አንድም ከተማ አያመልጥም። እግዚአብሔር ተናግሮአልና፣ሸለቆው ይጠፋል፤ዐምባውም ይፈርሳል።

9. በራ እንድታመልጥ፣ለሞዓብ ክንፍ ስጧት፤ከተሞቿም ምንም እስከማይኖርባቸው ድረስ፣ባድማ ይሆናሉ።

10. “የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያከናውን ርጉም ይሁን፤ሰይፉን ደም ከማፍሰስ የሚከላከል የተረገመ ይሁን፤

11. “ሞዓብ በአምቡላው ላይ እንዳረፈ የወይን ጠጅ፣ከልጅነት ጀምሮ የተረጋጋ ነበረ፤ከዕቃ ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፤በምርኮም አልተወሰደም፤ቃናው እንዳለ ነው፤መዐዛውም አልተለወጠም።

12. ስለዚህ ዕቃውን የሚገለብጡ ሰዎችን፤የምልክበት ጊዜ ይመጣል፤”ይላል እግዚአብሔር።“እነርሱም ይደፉታል፤ዕቃውን ባዶ ያስቀራሉ፤ማንቆርቆሪያዎቹንም ይሰባብራሉ።

13. የእስራኤል ቤት፤በቤቴል ታምኖ እንዳፈረ ሁሉ፣ሞዓብም በካሞሽ ያፍራል።

14. “እናንተ፣ ‘እኛ ተዋጊዎች ነን፤በጦርነትም ብርቱ ነን’ ልትሉ እንዴት ቻላችሁ?

15. ሞዓብ ትጠፋለች፤ ከተሞቿም ይወረራሉ፤ምርጥ ወጣቶቿም ወደ መታረድ ይወርዳሉ፤”ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ፤

16. “የሞዓብ ውድቀት ተቃርቦአል፤ጥፋቱም ፈጥኖ ይመጣበታል።

17. በዙሪያው የምትኖሩ ሁሉ፤ዝናውን የምታውቁ ሁሉ አልቅሱለት፤‘ብርቱው ከዘራ፣የከበረው በትር እንዴት ሊሰበር ቻለ’ በሉ።

18. “ሞዓብን የሚያጠፋ፣በአንቺ ላይ ይመጣልና፤የተመሸጉ ከተሞችሽንም ያጠፋልና፤አንቺ የዲቦን ሴት ልጅ ሆይ፣ከክብርሽ ውረጂ፣በደረቅም መሬት ተቀመጪ።

19. አንቺ በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ፤በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤የሚሸሸውን ወንድ፣ የምታመልጠውንም ሴት፣ምን ተፈጠረ?’ ብለሽ ጠይቂ።

20. ሞዓብ በመፍረሱ ተዋርዷል፤ዋይ በሉ፤ ጩኹ፤የሞዓብን መደምሰስ፣በአርኖን አጠገብ አስታውቁ።

21. ፍርድ በዐምባው ምድር፦በሖሎን፣ በያሳና በሜፍዓት ላይ፣

22. በዲቦን፣ በናባውና በቤት ዲብላታይም ላይ፣

23. በቂርያታይም፣ በቤት ጋሙልና በቤትምዖን ላይ፣

24. በቂርዮትና በባሶራ ላይ፤በሩቅና በቅርብ፣ ባሉት በሞዓብ ከተሞች ሁሉ ላይ መጥቶአል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 48