ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 43:6-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. በተጨማሪም ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን እንዲሁም የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን በአኪቃም ልጅ በጎዶልያስ እጅ የተዋቸውን የንጉሡን ሴቶች ልጆች፣ ነቢዩ ኤርምያስንና የኔርያን ልጅ ባሮክን ወሰዷቸው፤

7. የእግዚአብሔርንም ቃል ባለመታዘዝ ወደ ግብፅ ገቡ፤ ዘልቀውም እስከ ጣፍናስ ድረስ ሄዱ።

8. በጣፍናስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

9. “ትልልቅ ድንጋዮች ውሰድና በጣፍናስ ባለው የፈርዖን ቤተ መንግሥት በር ላይ የይሁዳ ሰዎች እያዩ በሸክላ ጡብ ወለል ውስጥ ቅበራቸው፤

10. እንዲህም በላቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አገልጋዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ ዙፋኑንም እዚህ በቀበርኋቸው ድንጋዮች ላይ እዘረጋለሁ፤ የንጉሥ ድንኳኑንም በላያቸው ይተክላል።

11. እርሱም መጥቶ ግብፅን ይወጋል፤ ሞት የሚገባቸውን ለሞት፣ ለምርኮ የተመደቡትን ወደ ምርኮ፣ ለሰይፍ የተዳረጉትን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል።

12. እርሱ የግብፅ አማልክት ቤተ ጣዖቶች ላይ እሳት ይለኵሳል፤ ያቃጥላቸዋልም፣ አማልክታቸውንም ማርኮ ይወስዳል። እረኛ ልብሱን እንደሚጐናጸፍ የግብፅን ምድር ተጐናጽፎ ከዚያ በሰላም ይሄዳል።

13. በግብፅ ምድር የሚገኙትን የፀሓይ አምላክ ቤተ ጣዖት ሐውልቶች ይሰባብራል፤ የግብፅንም አማልክት ቤተ ጣዖቶች በእሳት ያቃጥላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 43