ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 42:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ‘ባመጣሁባችሁ ጥፋት አዝኛለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፤ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።

11. አሁን የሚያስፈራችሁን የባቢሎንን ንጉሥ አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ ይላል እግዚአብሔር፤

12. እርሱ እንዲምራችሁና ወደ አገራችሁ እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ።’

13. “እናንተ ግን፤ ‘በዚህች ምድር አንቀመጥም’ ብትሉና አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባትታዘዙ፣

14. ደግሞም፣ ‘ጦርነት ወደማናይበት፣ የመለከት ድምፅ ወደማንሰማበትና ወደማንራብበት ወደ ግብፅ ምድር ሄደን በዚያ እንኖራለንጰ ብትሉ፣

15. እንግዲህ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ ግብፅ ለመሄድ ወስናችሁ እዚያ ለመቀመጥ ብትሄዱ፣

16. የፈራችሁት ሰይፍ በዚያ ያገኛችኋል፤ የሠጋችሁበት ራብ እስከ ግብፅ ድረስ ተከትሎአችሁ ይመጣል፤ በዚያም ትሞታላችሁ።

17. በዚያም ለመኖር ወደ ግብፅ ለመሄድ የወሰኑ ሁሉ በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር በእርግጥ ይሞታሉ፤ ከማመጣባቸውም ጥፋት አንድ እንኳ የሚተርፍ ወይም የሚያመልጥ አይገኝም።’

18. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ቍጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደ ፈሰሰ፣ እንዲሁ ወደ ግብፅ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ በእናንተ ላይ ይፈሳል፤ እናንተም የመነቀፊያና የድንጋጤ፣ የመረገሚያና የመዘባበቻ ምልክት ትሆናላችሁ፤ ይህንም ስፍራ ዳግመኛ አታዩም።’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 42