ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 4:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. እስከ መቼ የጦርነት ዐርማ እመለከታለሁ?እስከ መቼስ የመለከት ድምፅ እሰማለሁ?

22. “ሕዝቤ ተላሎች ናቸው፤እኔን አያውቁኝም።ማስተዋል የጐደላቸው፣መረዳትም የማይችሉ ልጆች ናቸው።ክፋትን ለማድረግ ጥበበኞች፤መልካም መሥራት ግን የማያውቁ።”

23. ምድርን ተመለከትሁ፤እነሆ ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች፤ሰማያትንም አየሁ፣ብርሃናቸው ጠፍቶአል።

24. ተራሮችን ተመለከትሁ፣እነሆ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ኰረብቶችም ሁሉ ተናጡ።

25. አየሁ፤ ሰው አልነበረም፤የሰማይ ወፎች ሁሉ በረው ጠፍተዋል።

26. ተመለከትሁ፤ እነሆም፣ ፍሬያማው ምድር በረሓ ሆነ፤ከተሞቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት፣ከብርቱ ቍጣው የተነሣ ፈራረሱ።

27. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፤ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም።

28. ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፤ሰማያትም በላይ ይጨልማሉ፤ተናግሬአለሁ፤ ሐሳቤን አልለውጥም፤ወስኛለሁ፤ ወደ ኋላም አልልም።

29. ከፈረሰኞችና ከቀስተኞች ጩኸት የተነሣ፣ከተማ ሁሉ ይሸሻል፤አንዳንዶች ደን ውስጥ ይገባሉ፤ሌሎችም ቋጥኝ ላይ ይወጣሉ፤ከተሞች ሁሉ ባዶ ቀርተዋል፤የሚኖርባቸውም የለም።

30. አንቺ ለጥፋት የተዳረግሽ ሆይ፤ ምን መሆንሽ ነው?ቀይ ቀሚስ የለበስሽው ለምንድ ነው?ለምን በወርቅ አጌጥሽ?ዐይኖችሽንስ ለምን ተኳልሽ?እንዲያው በከንቱ ተሽሞንሙነሻል፤የተወዳጀሻቸው ንቀውሻልና፤ነፍስሽንም ሊያጠፉ ይፈልጋሉ።

31. የበኵር ልጇን ለመውለድ እንደምታምጥ፣በወሊድ እንደምትጨነቅ ሴት ድምፅ ሰማሁ፤የጽዮን ሴት ልጅ ትንፋሽ አጥሮአት ስትጮኽ፣እጇን ዘርግታ፣“ወዮልኝ! ተዝለፈለፍሁ፣በነፍሰ ገዳዮች እጅ ወደቅሁ” ስትል ሰማሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 4